ወደ ዜና ይመለሱ

65ኛው የዩሪ ጋጋሪን የህዋ ጉዞ መታሰቢያ፡ 'የዩሪ ምሽት' በኢትዮጵያ በድምቀት ተከበረ!

65ኛው የዩሪ ጋጋሪን የህዋ ጉዞ መታሰቢያ፡ 'የዩሪ ምሽት' በኢትዮጵያ በድምቀት ተከበረ!

ከዛሬ 65 ዓመት በፊት ሚያዝያ 4 ቀን 1953 ዓ.ም. (እ.ኤ.አ. ኤፕሪል 12 ቀን 1961) ራሻዊው ዩሪ ጋጋሪን የሰው ልጅን የምድር ቆይታ ወሰን በማለፍ ወደ ህዋ በመጓዝ ምድርን በህዋ ውስጥ የዞረበት ታሪካዊ ቀን ነው። ይህ ስኬት የሰው ልጅ የህዋ ምርምር ስራዎች ትልቅ ማሳያ ተደርጎ የሚቆጠር ሲሆን፤ በየአመቱ ይህ ቀን ዓለም አቀፍ የኮስሞኖቲክስ ቀን እና 'የዩሪ ምሽት' (Yuri's Night) ተብሎ ይከበራል። የዘንድሮው 65ኛ አመት መታሰቢያም በሀገራችን በሁለት የተለያዩ ደማቅ መርሃ ግብሮች ተከብሮ ውሏል።

ከዛሬ 65 ዓመት በፊት ሚያዝያ 4 ቀን 1953 ዓ.ም. (እ.ኤ.አ. ኤፕሪል 12 ቀን 1961) ራሻዊው ዩሪ ጋጋሪን የሰው ልጅን የምድር ቆይታ ወሰን በማለፍ ወደ ህዋ በመጓዝ ምድርን በህዋ ውስጥ የዞረበት ታሪካዊ ቀን ነው። ይህ ስኬት የሰው ልጅ የህዋ ምርምር ስራዎች ትልቅ ማሳያ ተደርጎ የሚቆጠር ሲሆን፤ በየአመቱ ይህ ቀን ዓለም አቀፍ የኮስሞኖቲክስ ቀን እና 'የዩሪ ምሽት' (Yuri's Night) ተብሎ ይከበራል። የዘንድሮው 65ኛ አመት መታሰቢያም በሀገራችን በሁለት የተለያዩ ደማቅ መርሃ ግብሮች ተከብሮ ውሏል።

ምስል፡ በዩሩ ጋጋሪን የመታሰቢያ ሃውልት የአበባ ጉንጉን ሲቀመጥ

የጠዋቱ መርሃ ግብር፡ ዓለም አቀፍ የኮስሞኖቲክስ ቀን አከባበር

የ2018 ዓ.ም የኮስሞኖቲክስ ቀን የጠዋት መርሃ ግብር በስፔስ ሳይንስ እና ጂኦስፓሻል ኢንስቲትዩት (SSGI) እና በሩስያ ኤምባሲ ትብብር ተዘጋጅቶ በኢንስቲትዩቱ በሚገኘው የዩሪ ጋጋሪን መታሰቢያ ሀውልት ስር ተካሂዷል።

በዚህ መርሃ ግብር ላይ በኢትዮጵያ የሩሲያ አምባሳደር ኤቭጌኒ ተሬክሂን ተገኝተው የሩሲያ እና የኢትዮጵያ ታሪካዊ ግንኙነት በሳይንስና ቴክኖሎጂ ዘርፍ በተለይም በስፔስ ሳይንስ መስክ ያለውን ትብብር በማድነቅ፣ የዩሪ ጋጋሪን ስኬት የሰው ልጅ የጋራ ድል መሆኑን አውስተዋል።

ምስል፦ የሩሲያ አምባሳደር ኤቭጌኒ ተሬክሂን

በመቀጠልም የኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስ ሶሳይቲ (ESSS) ስራ አስኪያጅ አቶ ኪሩቤል መንበሩ ስለ ዩሪ ጋጋሪን ታሪካዊ ትሩፋት፣ ይህ ስኬት ለኢትዮጵያ ወጣቶች ስለሚሰጠው መነሳሳት እና ከዚሁ ታሪካዊ ክስተት ስለሚወሰዱ ትምህርቶች ሰፊ ንግግር እና ማብራሪያ አድርገዋል።

የኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስ ሶሳይቲ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ኪሩቤል መንበሩ

የጠዋቱ መታሰቢያ መርሃ ግብርም የክብር እንግዶች በዩሪ ጋጋሪን ማስታወሻ ሀውልት ስር የማስታወሻ አበባ የማስቀመጥ ስነ-ስርዓት በማካሄድ ተጠናቋል።

የከሰዓት በኋላ መርሃ ግብር፡ 'የዩሪ ምሽት' በሩሲያ ባህል ማዕከል

በሩሲያ የሳይንስ እና ባህል ማዕከል እና በኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስ ሶሳይቲ የጋራ አዘጋጅነት የተዘጋጀው 'የዩሪ ምሽት' ደግሞ ከሰዓት በኋላ እጅግ ደማቅ በሆነ መርሃ ግብር ተከብሮ ውሏል።

ሚያዝያ 7፣ 2018 ዓ.ም በሩሲያ የሳይንስ እና ባህል ማዕከል አዳራሽ በተካሄደው በዚህ ደማቅ ዝግጅት ላይ፣ መርሃ ግብሩን በይፋ ያስጀመሩት የ'ሩሲያ ሀውስ' ተወካይ ዲሚትሪ ቢሪልቬ እና የኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስ ሶሳይቲ ስራ አስኪያጅ አቶ ኪሩቤል መንበሩ ናቸው። ሁለቱም የስራ ሃላፊዎች ባደረጉት የመክፈቻ ንግግር የእለቱን ታሪካዊ ፋይዳ እና የህዋ ሳይንስን ማስተዋወቅ ያለውን ጠቀሜታ ለታዳሚው አስገንዝበዋል።

ምስል፦ የሩሲያ ሳይንስ እና ባህል ማዕከል ተወካይ ዲሚትሪ ቢሪልቬ

በእለቱ መርሃ ግብር ላይ በዘርፉ በተሰማሩ ሶስት ባለሙያዎች ሰፊ እና አዝናኝ ገለፃዎች ተደርገዋል። የአለም አቀፍ የስነ ፈለክ ህብረት (IAU) OAE NAEC ኢትዮጵያ ተወካይ አቶ ነብዩ ሱለይማን "ከስፑትኒክ እስከ ሶዩዝ፡ የሶቪየት ጉዞ ወደ የሰው ልጅ የህዋ በረራ" በሚል ርዕስ ታሪካዊ ዳራን ሲያብራሩ፤ የኢትዮጵያ አየር ሀይል አካዳሚ ቴክኒካል ኮሌጅ ተመራማሪ ዶ/ር (ሌተናል ኮሎኔል) ሙሉብርሃን ሀይሉ "ህዋ፡ እኛው ነን" በሚል ርዕስ ማራኪ ገለፃ አድርገዋል። እንዲሁም አማተር የስነ-ፈለክ ተመራማሪ እና የኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስ ሶሳይቲ በጎ ፈቃደኛ አቶ እስጢፋኖስ ወርቁ "ወደ ላይ መመልከት፣ ከዛም ባሻገር መድረስ" በሚል ርዕስ ያቀረቡት ትምህርታዊ ጽሁፍ የዝግጅቱ አካል ነበረ። ታዳሚዎችም ከነዚህ ባለሙያዎች ገለፃ ስለ ህዋ ምርምር ታሪክ እና አጽናፈ አለም አስገራሚ ሚስጥሮች ሰፊ ግንዛቤን መጨበጥ ችለዋል።

የዕለቱ አቅራቢዎች ፦ (ከግራ ወደ ቀኝ) ዶ/ር (ሌተናል ኮሎኔል) ሙሉብርሃን ሀይሉ ፣ አቶ ነብዩ ሱለይማን ፣ አቶ እስጢፋኖስ ወርቁ

የዝግጅቱ ሌላኛው ማራኪ ክፍል በሶስት የተለያዩ ትምህርት ቤቶች መካከል የተካሄደው የህዋ ሳይንስ ጥያቄና መልስ ውድድር ነበር። ተማሪዎቹ በህዋ ሳይንስ፣ በስነ-ፈለክ ታሪክ እና በዩሪ ጋጋሪን የህዋ ጉዞ ላይ ያላቸውን እውቀት የፈተኑበት ይህ ውድድር በታዳሚው ዘንድ ከፍተኛ መነቃቃትን እና ተሳትፎን ፈጥሮ ነበር።

ምስል፦ የጥያቄና መልስ ውድድር

የዘንድሮውን የዩሪ ምሽት ልዩ ያደረገው ክስተት ደግሞ የክብር እንግዳ የነበሩት ሩሲያዊው ኮስሞናት አሌክሳንደር ሰርጌቪች ግሬበንኪን በቪዲዮ ኮንፈረንስ አማካኝነት ከታዳሚዎች ጋር ያደረጉት ቀጥታ ቆይታ ነው። ከዩሪ ጋጋሪን የኮስሞናት ስልጠና ማዕከል የተጋበዙት እና በቅርቡ በስፔስ ኤክስ ተልዕኮ ወደ አለም አቀፉ የህዋ ጣቢያ አቅንተው የነበሩት ኮስሞናቱ፣ በህዋ ጣቢያው ውስጥ ስለነበራቸው ቆይታ እና ተልዕኮ ከተማሪዎች ለተነሳላቸው ጥያቄ ጥልቀት ያለው ማብራሪያ እና ምላሽ ሰጥተዋል። 

ምስል፦ የሩሲያ ኮስሞናውት አሌክሳንደር ሰርጌቪች ግሬበንኪን በበይነ መረብ ቪዲዮ ኮንፍረንስ ለተማሪዎች ምላሽ ሲሰጡ

በተጨማሪም ወደፊት ስለታቀዱት የጨረቃ ላይ ጉዞዎች ያብራሩ ሲሆን፤ ከታዳሚው በተለይም ከወጣቶች ለቀረቡላቸው አስገራሚ ጥያቄዎች ምላሽ ሰጥተዋል። በንግግራቸው ማጠቃለያም ለመጪው ትውልድ እና ለወደፊቱ የህዋ ተመራማሪዎች አነቃቂ ምክራቸውን ለግሰዋል።

ዝግጅቱ ከተለያዩ ትምህርት ቤቶች የተውጣጡ ተማሪዎች፣ የኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስ ሶሳይቲ አባላት፣ የህዋ ሳይንስ አፍቃሪያን እና ጥሪ የተደረገላቸው የክብር እንግዶች በተገኙበት እጅግ ደማቅ እና ትምህርት ሰጪ በሆነ መልኩ ተጠናቋል።

ሰዎች እነዚህንም ወደዋል