Back to News

ከሃያ ዓመቱ የመሪህ ጉዞ ይልቅ የአሥር ዓመቱ የጨረቃ ከተማ! - የኤሎን ማስክ አዲስ ስሌት

ከሃያ ዓመቱ የመሪህ ጉዞ ይልቅ የአሥር ዓመቱ የጨረቃ ከተማ! - የኤሎን ማስክ አዲስ ስሌት

ለባለፉት ሁለት አስርት ዓመታት የኤሎን ማስክ ብቸኛ ህልም እና የስፔስ ኤክስ ኩባንያ መተዳደሪያ ዓላማ አንድ ብቻ ነበር፦ የሰው ልጅን በመሪህ (Mars) ላይ ማስፈር! ነገር ግን እሁድ ዕለት ኢሎን በኤክስ ገጹ ላይ ባሰፈረው መልዕክት ዓለምን አስገርሟል።

ለባለፉት ሁለት አስርት ዓመታት የኤሎን ማስክ ብቸኛ ህልም እና የስፔስ ኤክስ ኩባንያ መተዳደሪያ ዓላማ አንድ ብቻ ነበር፦ የሰው ልጅን በመሪህ (Mars) ላይ ማስፈር! ነገር ግን እሁድ ዕለት ኢሎን በኤክስ ገጹ ላይ ባሰፈረው መልዕክት ዓለምን አስገርሟል።

ማስክ በኤክስ (X) ገጹ ላይ በቀጥታ እንዳሰፈረው፦

"ላልሰማችሁ፤ ስፔስ ኤክስ ከወዲሁ ትኩረቱን በጨረቃ ላይ ራሷን የምታሳድግ ከተማ በመገንባት ላይ አድርጓል። ምክንያቱም ይህንን ከ10 ዓመት ባነሰ ጊዜ ውስጥ ማሳካት የምንችል ሲሆን፣ መሪህ ግን ከ20 ዓመታት በላይ ይፈጅብናል።"

ለመሆኑ ለ20 ዓመታት "መሪህ! መሪህ!" ሲል የነበረው ቢሊየነር፣ በድንገት ሃሳቡን ወደ ጨረቃ ለምን ቀየረ? ከጀርባው ያሉትን ሦስት አበይት ምክንያቶች እንመልከት።

ምስል፦ ኤሎን ማስክ እና በx የማኅበራዊ ትሥሥር ገጹ ያጋራው ልጥፍ

1. የጊዜ እና የርቀት ስሌት (የሂሳቡ እውነት)

ማስክ እንዳለው፣ የሰው ልጅን ከምድር ውጭ በሌሎች ዓለማት ማስፈር የህልውና ጉዳይ ነው። የምድር ላይ የተፈጥሮ ወይም የሰው ሰራሽ አደጋ የሰው ልጅን ከማጥፋቱ በፊት በፍጥነት መንቀሳቀስ ያስፈልጋል። ለዚህ ደግሞ መሪህ በጣም ሩቅ እና አዝጋሚ ናት።

  • የመሪህ ፈተና፡ ወደ መሪህ መንኮራኩር ማምጠቅ የሚቻለው ምድር እና መሪህ ትክክለኛ ቦታ ላይ ሲሰለፉ በየ26 ወሩ (ከሁለት ዓመት ተኩል ገደማ በኋላ) ብቻ ነው። ጉዞውም 6 ወራት ይፈጃል። በዚህ ፍጥነት መሪህ ላይ ከተማ መገንባት ከ20 ዓመታት በላይ ይወስዳል።
  • የጨረቃው ብልጫ፡ ወደ ጨረቃ ግን በየ10 ቀኑ መንኮራኩር ማምጠቅ ይቻላል፤ ጉዞውም 2 ቀናት ብቻ ነው የሚፈጀው። ማስክ "ወደ ጨረቃ በፍጥነት በመመላለስ፣ ከ10 ዓመት ባነሰ ጊዜ ውስጥ ከተማ መገንባት እንችላለን" ብሏል።

2. የኤአይ እና የሳተላይት ዳታ ማዕከሎች እቅድ

ይህ የጨረቃ ላይ ከተማ እቅድ፣ ማስክ በቅርቡ ይፋ ካደረገው "የ1 ሚሊዮን ሳተላይቶች የዳታ ማዕከል" እቅድ ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት አለው።

ስፔስ ኤክስ የሰው ሰራሽ አስተውሎት ኩባንያ የሆነውን ኤክስ-ኤአይ መግዛቱ ይታወሳል። ማስክ የኤአይ ቴክኖሎጂን በኃይል ለመደገፍ፣ በህዋ ላይ ግዙፍ የኮምፒውተር ሰርቨሮችን መገንባት ይፈልጋል። ታዲያ ጨረቃ ለዚህ ትልቅ መፍትሄ ናት።

በጨረቃ ላይ ማምረቻ ፋብሪካዎችን በመገንባት፣ የጨረቃን የተፈጥሮ ሃብት ተጠቅሞ ሳተላይቶችን እዛው ማምረት ይቻላል። ከዚያም የጨረቃን ዝቅተኛ ስበት በመጠቀም በኤሌክትሮማግኔቲክ ማስፈንጠሪያ ሳተላይቶቹን በቀላሉ ወደ ጥልቅ ህዋ መተኮስ ይቻላል። ማስክ ይህ እርምጃ የሰው ልጅን በካርዳሼቭ ስኬል ወደሚቀጥለው የዕድገት ደረጃ እንደሚያሸጋግረው ያምናል።

በተጨማሪም ባለሃብቶችን ለማስደሰት፣ ጨረቃ ላይ መስራት ከመሪህ ይልቅ ቶሎ የገንዘብ ትርፍ ያስገኛል።

ምስል፦ የአርጤምስ ተልዕኮ እና ናሳ የተለመው የጨረቃ መንደር ፤ ምንጭ፦ ናሳ

3. የቢሊየነሮቹ ፉክክር፡ ጄፍ ቤዞስ እና ናሳ

ማስክ ትኩረቱን ወደ ጨረቃ ያደረገበት ሌላው ትልቅ ምክንያት የአማዞኑ መስራች ጄፍ ቤዞስ ነው። የቤዞስ የህዋ ኩባንያ የሆነው ብሉ ኦሪጅን፣ ለናሳ የአርጤምስ የጨረቃ ላይ ጉዞ ፕሮግራም መንኮራኩር ለመስራት ትልቅ ተፎካካሪ ሆኖ መጥቷል። ብሉ ኦሪጅን የህዋ ቱሪዝም ጉዞውን አቁሞ ሙሉ ትኩረቱን በጨረቃ ላይ አድርጓል።

በሌላ በኩል የስፔስ ኤክስ ግዙፍ ሮኬት ስታርሺፕ አሁንም በሙከራ ላይ ያለ እና በተደጋጋሚ የፈነዳ በመሆኑ፣ ናሳ የሰጠውን የጨረቃ ላይ ማረፊያ ኮንትራት በተባለው ጊዜ ላያደርስ ይችላል የሚል ስጋት ፈጥሮ ነበር። ስለዚህ ማስክ በተቀናቃኞቹ ላለመበለጥ ሲል ሙሉ ትኩረቱን ጨረቃ ላይ ማድረግ ግድ ሆኖበታል።

ምስል፦ የአማዞን ባለቤት እና ቢሊየነር ጄፍ ቤዞስ እና የሕዋ ኩባንያው ብሉ ኦሪጅን

ማጠቃለያ፡ መሪህ ተረሳች ማለት ነው?

ማስክ መሪህን ሙሉ በሙሉ አልረሳትም። "የመሪህ ከተማ ግንባታም ከ5 እስከ 7 ዓመታት ውስጥ ይጀመራል፤ ከጨረቃ ጋር ትይዩ ይሰራል" ብሏል። ነገር ግን፣ የሰው ልጅ የመጀመሪያዋ የህዋ ላይ ከተማ መሪህ ሳትሆን ጨረቃ እንደምትሆን አሁን በይፋ ተረጋግጧል።

ከዚህ በፊት ጨረቃን "ትኩረት አሳች" ብሎ ሲጠራት የነበረው ማስክ፣ አሁን የሰው ልጅን ከጥፋት ማዳኛ እና የቴክኖሎጂ ማሸጋገሪያ ዋነኛ መድረክ አድርጓታል።

People Also Like