አርጤምስ 2 ጠፈርተኞችን ይዞ በጨረቃ ዙሪያ ያደረገውን ታሪካዊ ጉዞ በተሳካ ሁኔታ አጠናቆ ወደ መሬት ተመልሷል። ይህ ስኬት ለሰው ልጅ የጠፈር ምርምር ትልቅ ምዕራፍ ቢሆንም፣ የናሳ (NASA) ዋና ትኩረት አሁን ወደ ቀጣዩ እና እጅግ ግዙፍ ወደሆነው እቅድ ዞሯል። ይህ እቅድ እ.ኤ.አ በ1960ዎቹ ከነበረው የጠፈር ሽሚያ ፍጹም የተለየ ነው፤ ምክንያቱም አሁን ግቡ ባንዲራ ተክሎ መመለስ ሳይሆን፣ በጨረቃ ላይ ቋሚ ሰፈር ገንብቶ መቆየት ነው። ከቻይና ጋር ያለውን የጠፈር ሽሚያ ለማሸነፍ ናሳ አሮጌውን አሰራር በመተው አዲስ ስልት ነድፏል።
"ኢግኒሽን" (Ignition) በሚል በተጠራው አዲስ መርሃ ግብር፣ ናሳ በአሜሪካ ብሔራዊ የጠፈር ፖሊሲ ላይ በመመስረት የሰውን ልጅ በጨረቃ ላይ በቋሚነት ለማስፈር እና ወደ ማርስ ለሚደረገው ጉዞ መሰረት የሚጥሉ አስደናቂ እቅዶችን ይፋ አድርጓል። የናሳ ዋና አስተዳዳሪ ጃሬድ አይዛክማን እንደገለጹት፣
"ግንባታው ከተጠናቀቀ በኋላ፣ ወደ ጨረቃ መመለስ እና ማዕከል መገንባት በቀጣይ ከምናስመዘግባቸው ድሎች ጋር ሲነጻጸር ቀላል ሆኖ ይታያል።"

የናሳ ዋና አስተዳዳሪ ጃሬድ አይዛክማን
ቀጣዮቹ የአርጤምስ ተልዕኮዎች (ከጨረቃ ማዕከል ግንባታ በፊት)
በቀድሞው የናሳ እቅድ መሰረት አርጤምስ 3 ሰዎችን በቀጥታ በጨረቃ ላይ ያሳርፋል ተብሎ የነበረ ቢሆንም፣ ይህ ሂደት ከፍተኛ ስጋት ስለነበረው ተቀይሯል።
የማምጠቅ ሂደቱን ለማፋጠን እና ደህንነትን ለማረጋገጥ፣ አርጤምስ 3 (እ.ኤ.አ በ2027 የሚመጠቀው) በቀጥታ ወደ ጨረቃ አይሄድም። በምትኩ በመሬት ዝቅተኛ ምህዋር (Low Earth Orbit) ላይ በመቆየት፣ የኦርዮን (Orion) መንኮራኩር እና በስፔስ ኤክስ እና ብሉ ኦሪጂን የሚፈበረኩትን የጨረቃ ላይ ማረፊያ ሞጁሎችን በማገናኘት የተግባር ልምምድ ያደርጋል። ጠፈርተኞቹ አዲሱን የጠፈር ልብስ (EVA suits) እና የህይወት ድጋፍ ስርአቶችን በቅርበት ይሞክራሉ። ይህ ተልዕኮ ለአርጤምስ 4 እንደ ቅድመ ልምምድ ይወሰዳል።

የናሳ የሰው ልጅ ማረፊያ ስርዓት (HLS) ንድፍ ምስል፦ በግራ በኩል የስፔስ ኤክስ (SpaceX) ማረፊያ ሞጁል መሬትን ከጀርባው አድርጎ በጨረቃ ላይ ሲታይ፤ በቀኝ በኩል ደግሞ የብሉ ኦሪጂን 'ብሉ ሙን' (Blue Moon) መንኮራኩር እና አንድ ጠፈርተኛ አጠገቡ ስራ ላይ ሆኖ ያሳያል።
የጨረቃ ላይ ማዕከል ግንባታ፡ ዝርዝር ምዕራፎች
የጌትዌይ የጠፈር ጣቢያ ፕሮግራም ለጊዜው እንዲቆም ተደርጎ፣ ናሳ ለጨረቃ ማዕከል ግንባታ 20 ቢሊዮን ዶላር በጀት መድቧል። ይህ ግንባታ በሚከተሉት ዝርዝር እና ሰፊ ሶስት ዋና ዋና ምዕራፎች ይከፈላል፦
ምዕራፍ 1፡ ግንባታ፣ ሙከራ እና ልምድ መቅሰም (እ.ኤ.አ 2026 - 2028)
የሚያካትታቸው ተልዕኮዎች፡ አርጤምስ 4 እና አርጤምስ 5
ይህ ምዕራፍ ዋና ዓላማው ወደ ጨረቃ ገጽ አስተማማኝ እና ተከታታይ ጉዞዎችን ማድረግ ነው። በአጠቃላይ 25 የማምጠቅ እና 21 የማሳረፍ ተልዕኮዎች ይኖሩታል። ሰዎችን በጨረቃ ላይ የማሳረፉ ታሪካዊ ስራ በአርጤምስ 4 (እ.ኤ.አ በ2028 መጀመሪያ) የሚከናወን ሲሆን፣ አርጤምስ 5 ደግሞ እ.ኤ.አ በ2028 መገባደጃ ላይ ይከተላል። የናሳ ግብ እንደ አፖሎ ዘመን በየ 6 ወሩ ጠፈርተኞችን ማመላለስ ነው።
በዚህ ምዕራፍ የሚሰሩ ዋና ዋና ስራዎች፡
- የኑክሌር ሙቀት ሰጪዎች (RTGs)፡ ሁለት ሳምንት በሚረዝመው እና የሙቀት መጠኑ እስከ -200 ዲግሪ ሴንቲግሬድ በሚወርድበት የጨረቃ ሌሊት ኤሌክትሮኒክስ መሳሪያዎች እንዳይቀዘቅዙ እና እንዳይበላሹ የፕሉቶኒየም ኑክሌር ሙቀት ሰጪዎችን መጠቀም ይጀመራል።
- ቫይፐር (VIPER) ሮቨር፡ እ.ኤ.አ በ2027 በብሉ ኦሪጂን (Blue Origin) መንኮራኩር አማካኝነት ወደ ጨረቃ ደቡብ ዋልታ በማምራት ውሃ፣ በረዶ እና ሌሎች ጠቃሚ ማዕድናትን ያጠናል/ያሰሳል።
- መጓጓዣ እና ድሮኖች፡ ጠፈርተኞች የሚያሽከረክሩት እና ራሱን ችሎ የሚሄድ እስከ 900 ኪ.ሜ መጓዝ የሚችል የጨረቃ ላይ ተሽከርካሪ (LTV) ይሰማራል። ለመድረስ አስቸጋሪ የሆኑ ቦታዎችን (የተራራ ጫፎች እና ጥልቅ ጓድጓዶች) ለመቃኘት ደግሞ በሮኬት ሞተር የሚሰሩ ድሮኖች ይላካሉ።
- የመገናኛ ሳተላይቶች፡ 500 ሜጋባይት በሰከንድ (500 MB/s) ማስተላለፍ የሚችሉ ሳተላይቶች ምህዋር ላይ የሚቀመጡ ሲሆን፣ ሁሉም ሮቨሮች እና ድሮኖች የጨረቃ ላይ ቆይታቸውን በቀጥታ ስርጭት (Live Stream) ወደ መሬት ያስተላልፋሉ።

ይህ ሥዕላዊ መግለጫ (የኪነ-ጥበብ ባለሙያ ንድፍ) የብሉ ኦሪጂንን (Blue Origin) 'ብሉ ሙን ማርክ 1' ማረፊያ መንኮራኩር እና የናሳን 'ቫይፐር' (VIPER) የተሰኘ አሳሽ ሮቨር በጨረቃ ገጽ ላይ ያሳያል።
ምዕራፍ 2፡ የመጀመሪያ ደረጃ መሠረተ ልማት (እ.ኤ.አ 2029 - 2032)
የሚያካትታቸው ተልዕኮዎች፡ ከ አርጤምስ 6 እስከ አርጤምስ 13 (የ6 ወር ቋሚ ተልዕኮዎች)
ይህ ምዕራፍ መሠረተ ልማት የመዘርጋት እና ለቋሚ ቆይታ መሰረት የመጣል ስራዎችን ያካትታል። 27 የማምጠቅ እና 24 የማሳረፍ ስራዎች ይከናወኑበታል።
በዚህ ምዕራፍ የሚሰሩ ዋና ዋና ስራዎች፡
- ግዙፍ ቁፋሮ እና ግንባታ፡ ስድስት አዳዲስ ሮቨሮች ወደ ጨረቃ የሚላኩ ሲሆን፣ እነዚህ ሮቨሮች ድንጋይ ማጓጓዝ፣ መሬት ማስተካከል፣ ለኬብል እና ለቧንቧ የሚሆኑ ጉድጓዶችን መቆፈር ይችላሉ።
- ግፊቱ የተስተካከለ ሮቨር (Pressurised Rover)፡ ከጃፓን የጠፈር ኤጀንሲ (JAXA) እና ከቶዮታ ኩባንያ ጋር በመተባበር 15,000 ኪሎግራም የሚመዝን ግዙፍ ተሽከርካሪ ይላካል። ጠፈርተኞች የጠፈር ልብስ ሳይለብሱ (በቲሸርት ብቻ) በውስጡ መኖር ይችላሉ። ይህ "ተንቀሳቃሽ አፓርታማ" በሰዓት 3.5 ኪ.ሜ እየተጓዘ ለ10 ዓመታት ያገለግላል፤ በጨለማ ውስጥም ለ150 ሰዓታት መጓዝ ይችላል።
- የኃይል አቅርቦት፡ ረዣዥም ምሰሶዎች ላይ የሚገጠሙ ግዙፍ የፀሀይ ኃይል መሰብሰቢያዎች እና ትላልቅ ባትሪዎች ይተከላሉ። በተጨማሪም በመቶዎች የሚቆጠር ዋት ማመንጨት የሚችሉ የኑክሌር ፊዥን ሪአክተሮች (Nuclear fission reactors) ተተክለው ለተለያዩ ማዕከላት ኃይል ያከፋፍላሉ።

ግፊቱ የተስተካከለ ሮቨር በጨረቃ ገጽ ላይ ሲጓዝ የሚያሳይ ሥዕላዊ መግለጫ።
ምዕራፍ 3፡ የረጅም ጊዜ የሰው ልጅ ቆይታ (እ.ኤ.አ 2033 እና ከዚያ በኋላ)
የሚያካትታቸው ተልዕኮዎች፡ አርጤምስ 14 እና ቀጣይ ተልዕኮዎች
ይህ የጨረቃ ማዕከል (Artemis Moon Base) ሙሉ በሙሉ አገልግሎት የሚሰጥበት እና ቋሚ የሰው ልጅ መኖሪያ ዕውን የሚሆንበት ምዕራፍ ነው።
በዚህ ምዕራፍ የሚሰሩ ዋና ዋና ስራዎች፡
- ቋሚ መኖሪያ ቤቶች እና ከባድ ተሽከርካሪዎች፡ ከጣሊያን የጠፈር ኤጀንሲ (ASI) ጋር በመተባበር ትላልቅ የተያያዙ መኖሪያ ቤቶች (በመሬት ምህዋር ላይ እንደሚገኘው ዓለም አቀፍ የጠፈር ጣቢያ) ሲተከሉ፣ ከካናዳ የጠፈር ኤጀንሲ (CSA) ደግሞ የጨረቃ ላይ ከባድ ተሽከርካሪ (Lunar Utility Vehicle) ይላካል። 4 አባላት ያሉት የጠፈርተኞች ቡድን በአንድ ተልዕኮ እስከ 28 ቀናት (እና ከዚያ በላይ) በጨረቃ ላይ ይቆያል። በየወሩ 8,000 ኪሎግራም ምግብ፣ ውሃ እና አየር ከመሬት ይላክላቸም።
- ሀብትን መጠቀም (ISRU)፡ ከጨረቃ ላይ ከሚገኘው በረዶ ውስጥ ውሃ በማውጣት፣ ውሃውን በመበተን ለመተንፈሻ የሚሆን ኦክስጂን እና ለሮኬት ነዳጅ የሚሆን ሃይድሮጅን ማምረት ይጀመራል።
- የ3D ህትመት ግንባታ፡ የጨረቃን አቧራ በከፍተኛ ሙቀት በማቅለጥ ኮንክሪት የሚሰራ ሲሆን፣ በ3D ህትመት (3D printing) ቴክኖሎጂ አማካኝነት እውነተኛ እና ቋሚ ህንጻዎች በጨረቃ ላይ ይገነባሉ።

ምዕራፍ ሦሥትን የሚያሳይ የኪነ-ጥበብ ባለሙያ ምናባዊ ምስል
ዓለም አቀፍ የጠፈር ጣቢያ እና የግል ምህዋር
ከ20 ዓመታት በላይ ሲያገለግል የቆየው ዓለም አቀፍ የጠፈር ጣቢያ ለዘላለም ሊያገለግል አይችልም። በመሆኑም፣ ናሳ በመሬት ዝቅተኛ ምህዋር ላይ ያለውን የአሜሪካን ተሳትፎ ላለማቋረጥ አዲስ ስልት ነድፏል። በዚህም መሰረት፣ ናሳ በመንግስት የሚተዳደር ዋና ሞጁል ከነባሩ የጠፈር ጣቢያ ጋር በማገናኘት የግል ኩባንያዎች የራሳቸውን ሞጁሎች እንዲያክሉ እና የግል የጠፈር ጣቢያዎችን እንዲያሳድጉ ያደርጋል።
ወደ ማርስ በኑክሌር ኃይል
ከናሳ አስገራሚ አዳዲስ እቅዶች ውስጥ አንዱ የኑክሌር ኃይልን ወደ ጥልቅ ህዋ ማምጣት ነው። "ስፔስ ሪአክተር-1 ፍሪደም" የተሰኘው በኑክሌር ኃይል የሚንቀሳቀስ የመጀመሪያው የጠፈር መንኮራኩር እ.ኤ.አ ከ2028 በፊት ወደ ማርስ ይላካል። ይህ መንኮራኩር ቀይዋ ፕላኔት ማርስ ላይ ሲደርስ "ስካይፎል" የተባሉ ሄሊኮፕተሮችን በማሰማራት አስገራሚ ምርምሮችን ያደርጋል። የኑክሌር ኤሌክትሪክ ሞተር ቴክኖሎጂው ከጁፒተር ባሻገር ለሚደረጉ ጥልቅ የህዋ ምርምሮች ትልቅ አቅም ይፈጥራል።

የናሳ 'ኤስ.አር-1 ፍሪደም' (SR-1 Freedom) የጠፈር መንኮራኩር ከማርስ ፕላኔት ፊት ለፊት ሲታይ የሚያሳይ ሥዕላዊ መግለጫ።
ማጠቃለያ
አርጤምስ 2 ያመጣው ስኬት የናሳን አዲስ ትውልድ የጠፈር ጉዞ በይፋ አስጀምሯል። ምንም እንኳን እነዚህ ግቦች "የማይቻሉ" ቢመስሉም፣ ናሳ ሆን ብሎ ይህንን ከባድ ፈተና የተቀበለው ቀጣዩን ትውልድ ለማነሳሳት ነው። ናሳ የውስጥ ሰራተኞቹን አቅም በማጠናከር፣ ኮንትራክተሮችን ወደ ቋሚ የፌደራል ሰራተኝነት በመቀየር፣ እና ከዓለም አቀፍ አጋሮቹ ጋር በመተባበር የሰውን ልጅ በጨረቃ ላይ በቋሚነት ለማስፈር እየሰራ ይገኛል። የናሳ ተባባሪ አስተዳዳሪ አሚት ክሻትሪያ እንዳሉት፣ "ይህ እርምጃ ጉዟችንን ማዘግየት ሳይሆን፣ ይበልጥ ማፋጠን እና ትክክለኛ በሆኑ ነገሮች ላይ ትኩረት ማድረግ ነው።"
የሰው ልጅ ወደ ጨረቃ ገጽ ተመልሶ ቋሚ ሰፈር የሚገነባበት ጊዜ አሁን የዓመታት ሳይሆን የወራት ጉዳይ እየሆነ መጥቷል!