ወደ ጦማር ይመለሱ

ሳይንስ ፆታ የለውም

ሳይንስ ፆታ የለውም

እ.ኤ.አ. በ1915 ዝነኛው የሒሳብ ሊቅ እና የጎቲንገን ዩኒቨርሲቲ ፕሮፌሰር የነበረው ዴቪድ ሒልበርት፣ አንዲት ሴት በዩኒቨርሲቲው ውስጥ መምህር ሆና እንዳትቀጠር አጥብቀው ለተቃወሙት ባልደረቦቹ የሚከተለውን አስቂኝ እና ምልከታን የሚቀይር ምላሽ ሰጥቶ ነበር፦

"የአመልካቹ ጾታ ለቅጥር እንቅፋት የሚሆንበት ምንም አይነት ምክንያት አይታየኝም። እኛ ያለነው በዩኒቨርሲቲ ውስጥ እንጂ በሕዝብ መታጠቢያ ቤት ውስጥ አይደለም!"

ፕሮፌሰር ሒልበርት ይህንን የተናገረው አልበርት አይንስታይን ሳይንቲፊክ በሆነ መንገድ "ታላቅ የሒሳብ ሊቅ" ብሎ የጠራትን ኤሚ ኖይዘርን ወደ ሒሳብ ትምህርት ክፍሉ ለማምጣት ሲታገል ነበር። 

”Do not see that the sex of the candidate is an argument against her admission. We are a University, not a Bath House.” ምንጭ፦ https://network.febs.org/posts/33574

የሳይንስ ታሪክ ብዙ ጊዜ የሰው ልጅን ግማሽ ክፍል ባገለለ መልኩ ሲተረክ ይስተዋላል። ይሁን እንጂ ሴቶች ከዲኤንኤ (DNA) መዋቅር ጀምሮ እስከ ጋላክሲዎች ድረስ ለጽንፈ ዓለም ያለንን ግንዛቤ በመገንባት ረገድ መሰረታዊ ሚና ተጫውተዋል። ይህ ጽሑፍ የሴቶችን የሳይንስ ጉዞ፣ ያለፉባቸውን መሰናክሎች እና አሁንም የሚቀሩ ስራዎችን በወፍበረር ይዳስሳል።

የጥንት ፈርቀዳጆች: የሴቶች ሚና ባለፈው ዘመን

ለብዙ ክፍለ ዘመናት ሴቶች መደበኛ ትምህርት ተከልክለው ወይም ለሰሩት ስራ እውቅና ሳይሰጣቸው በከፍተኛ ተጋድሎ ለሳይንስ አስተዋጽኦ አድርገዋል። ብዙዎቹ እንደ ረዳት ወይም እንደ "ሰው ሰራሽ ኮምፒውተሮች" ተቆጥረው ይሰሩ ነበር። ለምሳሌ ያህል ጥቂቶቹን ለመጥቀስ ሂፓቲያ ኦፍ አሌክሳንድሪያ (Hypatia of Alexandria) በግብፅ በመጀመሪያ ደረጃ በታሪክ ከተመዘገቡ ሴት የሒሳብ እና የስነ-ፈለክ ምሁራን አንዷ ናት። በ19ኛው ክፍለ ዘመን መገባደጃ ላይ እንደ አኒ ጃምፕ ካነን እና ሄንሪታ ስዋን ሌቪት ያሉ ሴቶች የስነ-ፈለክ መረጃዎችን በመተንተን ትልቅ ስራ ሰርተዋል። ሌቪት የጋላክሲዎችን ርቀት ለመለካት የሚያስችል ቀመር ማግኘቷ ይታወቃል። ማሪ ኩሪ (Marie Curie) በሁለት የተለያዩ የሳይንስ ዘርፎች (ፊዚክስ እና ኬሚስትሪ) የኖቤል ሽልማትን በማሸነፍ የመጀመሪያዋ ሰው ናት። ስለ ራዲዮአክቲቪቲ (Radioactivity) ያደረገችው ምርምር ዛሬም ድረስ ለሴት ሳይንቲስቶች እንደ ትልቅ አርአያነት ይጠቀሳል።

https://cbr.ubc.ca/bridging-the-gap-challenges-for-women-in-science-and-academia/ ምስል ምንጭ፦ www.mobio.com

የ20ኛው ክፍለ ዘመን አጋማሽ፦ የሳይንስ እና የማህበራዊ ለውጥ ሽግግር

ይህ የታሪክ ምዕራፍ (በተለይም ከ1945 እስከ 1970 ያሉት ዓመታት) ሳይንስ ጥቂት "ባለሥልጣን ወንዶች" ብቻ ከሚሳተፉበት ስብስብ ወደ ተቋማዊ እና ዓለም አቀፋዊ ሙያ የተሸጋገረበት ወቅት ነበር። ለሴቶች ደግሞ ይህ ወቅት ካለክፍያ ረዳትነት ወይም ከመረጃ ተንታኝነት (Data Processors) ወጥተው ወደ ዋና ተመራማሪነት እና ወደ ምሁራዊ መሪነት የተሸጋገሩበት "አብዮታዊ" ምዕራፍ ነው። በ20ኛው ክፍለ ዘመን አጋማሽ ላይ ሴቶች ከመረጃ ተንታኝነት ወደ ዋና ተመራማሪነት በመሸጋገር የሳይንስን ዓለም ቀይረውታል። 

ዋትሰን እና ክሪክ የዲኤንኤን መዋቅር በማግኘታቸው ቢታወቁም፣ ሮዛሊንድ ፍራንክሊን ያነሳችው "Photo 51" የተሰኘው የኤክስሬይ ምስል ለዚህ ግኝት ዋናው እና ወሳኙ ማስረጃ ነበር። እንደ ካተሪን ጆንሰን እና ዶሮቲ ቮን ያሉ ሴቶች የመጀመሪያዎቹ አሜሪካውያን ወደ ጠፈር እንዲመነጠቁ እና ጨረቃ ላይ እንዲያርፉ ያስቻለውን ውስብስብ የሒሳብ ስሌት የሰሩ የተደበቁ ዋልታዎች ነበሩ። ሴሲሊያ ፔይን-ጋፖሽኪን (Cecilia Payne-Gaposchkin) ከዋክብት በዋነኝነት የተገነቡት ከሃይድሮጅን እና ከሂሊየም መሆኑን አረጋግጣለች። ይህ ግኝቷ በመጀመሪያ በወንድ ባልደረቦቿ ተቀባይነት ተነፍጎት የነበረ ቢሆንም፣ ቆይቶ ግን በሥነ-ፈለክ ታሪክ ውስጥ "እጅግ አስደናቂው የፒኤችዲ (PhD) ጥናት" ተብሎ ሊመሰከርለት ችሏል።

ለናሳ የጠፈር ተልእኮዎች ስኬት ወሳኝ ሚና የተጫወቱት ፈርቀዳጅ ሴት ሳይንቲስቶች እና መሐንዲሶች። ምስል ምንጭ፦ https://www.history.com/articles/human-computers-women-at-nasa

ከአብዮቱ በኋላም የሚታዩ ተግዳሮቶች

ምንም እንኳን "አብዮቱ" ለብዙዎች በሩን ቢከፍትም፣ መረጃዎች እንደሚያሳዩት "የሚሾልኩ ቧንቧዎች" (Leaky Pipeline) አሁንም ዓለም አቀፋዊ ፈተና ሆነው ቀጥለዋል። "Leaky Pipeline" የሚለው ቃል በሳይንስ፣ ቴክኖሎጂ፣ ኢንጂነሪንግ እና ሒሳብ (STEM) ዘርፎች ውስጥ ሴቶች በትምህርት እና በሥራ ሂደት ውስጥ እያሉ በየደረጃው የሚቀንሱበትን ወይም መስኩን ትተው የሚወጡበትን ክስተት ለመግለጽ ጥቅም ላይ የሚውል ዘይቤያዊ አነጋገር ሲሆን ይህ ክፍተት በየአገራቱ እና በየሳይንስ ዘርፎቹ ይለያያል።

ከ2015 እስከ 2018 ባሉት ዓመታት 107 አገራትን በማካተት የዩኔስኮ (UNESCO) የስታቲስቲክስ ተቋም ባጠናቀረው መረጃ መሠረት፤ በዓለም አቀፍ ደረጃ ከጠቅላላው ተመራማሪዎች መካከል የሴቶች ድርሻ 33.3% ብቻ ነው። ምንም እንኳን በአንዳንድ የህይወት ሳይንስ (Life Sciences) ዘርፎች የጾታ እኩልነት ቢታይም፣ እንደ ኢንጂነሪንግ፣ ፊዚክስ እና ኮምፒውተር ሳይንስ ባሉ ሳይንሶች ላይ አሁንም የወንዶች የበላይነት ይስተዋላል። ይህ በአብዛኛው የሚመነጨው ማህበረሰቡ ለሴቶች ካለው የተሳሳተ አመለካከት እና ሴት ልጆች ከታች ጀምሮ የሒሳብ ትምህርቶችን እንዳይከታተሉ ከሚደረግ ተጽዕኖ ነው። ክፍተቱ ይበልጥ ጎልቶ የሚታየው የተለያዩ የትምህርት ዘርፎችን ስናነጻጽር ነው። ለምሳሌ ሴቶች በባዮሎጂ እና በሕክምና ዘርፍ ከግማሽ በላይ የሚሆነውን ድርሻ ቢይዙም፣ በኮምፒውተር ሳይንስ እና በፊዚክስ ያላቸው ድርሻ ግን ከ 20% በታች ነው። ይህም የሚያሳየው አንድ የትምህርት ዘርፍ "ልዩ ተሰጥኦ" የሚጠይቅ ተደርጎ በተወሰደ ቁጥር የሴቶች ተሳትፎ እየቀነሰ እንደሚሄድ ነው።

በዓለም አቀፍ እና በአፍሪካ ደረጃ ያለውን ዝቅተኛ የሴት ተመራማሪዎች ድርሻ እንዲሁም በሳይንስ ዘርፎች መካከል ያለውን ከፍተኛ ልዩነት የሚያሳይ ግራፍ።

በአፍሪካ ተግዳሮቶቹ ዘርፈ ብዙ ናቸው። ምንም እንኳን እንደ ደቡብ አፍሪካ እና ግብፅ ያሉ አገራት የተሻለ ተሳትፎ ቢያሳዩም፣ በአህጉሪቱ ያለው የሴት ተመራማሪዎች አማካይ ድርሻ 30% አካባቢ ነው። ለዚህም እንደ ዋና ምክንያት የሚጠቀሱት ከፍተኛ የምርምር መሰረተ-ልማቶች እጥረት፣ የሴት መሪዎች (Mentors) አነስተኛ መሆን እና የቤት ውስጥ ስራ ጫናዎች ከምርምር ስራ ጋር መጋጨታቸው ነው። 

በዩኔስኮ (UNESCO) መረጃ መሠረት በሰሃራ በታች ባሉ የአፍሪካ አገራት ያለውን የሴት ተመራማሪዎች ድርሻ (31.5%) ከዓለም አቀፍ አማካይ እና ከሚፈለገው የእኩልነት ደረጃ (50%) ጋር በማነፃፀር የሚያሳይ ግራፍ

በሥነ-ፈለክ ዘርፍ የሴቶች ውክልና እየተሻሻለ ቢመጣም፣ በከፍተኛ የአመራር ደረጃዎች ላይ ግን አሁንም ዝቅተኛ ነው። ዛሬ ከዓለም አቀፉ የሥነ-ፈለክ ማህበር (IAU) አባላት መካከል ሴቶች 20% ብቻ ናቸው። 

የወደፊት ዕጣ ፈንታችን

በቤተ-ሙከራ ውስጥ "ፈቃድ ከማግኘት" ወደ "ቤተ-ሙከራውን መምራት" መሸጋገር የዘመናችን ትልቁ ስኬት ነው። የሩቅ ጋላክሲዎችን ብርሃን ብትመረምሩ ወይም ለአካባቢያችሁ ማህበረሰብ መፍትሄ የሚሆን ቴክኖሎጂ ብትፈጥሩ፣ የእናንተ ድምፅ የለውጥ ሞተር ነው። ይድረስ ለሚቀጥለው ትውልድ ሴት ሳይንቲስቶች፦ የእናንተ እይታ ለሳይንስ እድገት እጅግ በጣም ወሳኝ ነው። ሳይንስ መረጃዎችን መሰብሰብ ብቻ ሳይሆን፣ ትክክለኛውን ጥያቄ የመጠየቅ ጥበብም ጭምር ነው። ሴቶች ሲገለሉ፣ ዓለም አዳዲስ የችግር መፍቻ መንገዶችን ታጣለች። እንደ መዝጊያ፣ ወደ ጠፈር የሄደችው የመጀመሪያዋ ጥቁር አሜሪካዊት ዶ/ር ሜይ ጀሚሰን የተናገረችውን ታላቅ ምክር እናስታውስ፦

"ማንም ሰው ምናባችሁን፣ ፈጠራችሁን ወይም የማወቅ ጉጉታችሁን እንዲቀማችሁ አትፍቀዱ። ይህ በዓለም ላይ የእናንተ ቦታ ነው፤ ህይወታችሁም ነው።" ዶ/ር ሜይ ጀሚሰን (ወደ ጠፈር የሄደች የመጀመሪያዋ ጥቁር አሜሪካዊት)  

"ማንም ሰው ምናባችሁን፣ ፈጠራችሁን ወይም የማወቅ ጉጉታችሁን እንዲቀማችሁ አትፍቀዱ። ይህ በዓለም ላይ የእናንተ ቦታ ነው፤ ህይወታችሁም ነው።" ዶ/ር ሜይ ጀሚሰን (ወደ ጠፈር የሄደች የመጀመሪያዋ ጥቁር አሜሪካዊት)

🔗 Sources

Curie, E. (1937). Madame Curie: A Biography. Shetterly, M. L. (2016). Hidden Figures: The American Dream and the Untold Story of the Black Women Mathematicians Who Helped Win the Space Race. Rossiter, M. W. (1993). The Matthew Matilda Effect in Science. UNESCO Science Report (2021). To be smart, the digital revolution will need to be inclusive.

ሰዎች እነዚህንም ወደዋል