Back to Blog

2023 SY20 — የኢትዮጵያ የመጀመሪያው የምልምል አስቴሮይድ ግኝት

2023 SY20 — የኢትዮጵያ የመጀመሪያው የምልምል አስቴሮይድ ግኝት

ሰዎች ብዙውን ጊዜ በሰማይ ላይ አእዋፍትን፣ አውሮፕላንን ወይም አለፍ ሲል ተወርዋሪ ኮከብ በአጠገባቸው ብልጭ ድርግም እያሉ ማለፋቸውን ለማየት ጓጉተው ይጠብቃሉ፤ ነገር ግን በህዋ ውስጥ ዓይናችን ከሚያየው በላይ አእምሮን የሚፈትኑ ከዚህም በላይ ብዙ ጥልቅ እንቆቅልሾች እና ትንግርት የሆኑ ነገሮች ይገኛሉ።

ለዘመናት፣ የስነ ፈለክ ተመራማሪዎች የሚችሉትን ሁሉ ፍንጭ እየሰበሰቡ ከበላያችን የሚገኘውን ይህን ግዙፍ አጽናፈ አለም ለመረዳት በማንበብ እና መረጃ በመሰብሰብ ላይ ቆይተዋል። ጨረቃ ልክ እንደ ምድር ከድንጋይና ከአፈር የተሰራች መሆኗን ቢታወቅም፤ እንደ ምድር ውሃና የህይወት እስትንፋስ መጉደሉ ይታያል። በጊዜ ሂደትም፣ ፀሐይም ፍፁም በሆነ መልኩ ሳያቋርጥ ለዘመናት የሚነድ ፍጹም የእሳት ሉል ብቻ ሳትሆን ነቁጠፀሃይ (sun spots) ያሏትና የእሳት ነበልባሎች (flames) ከገጿ የሚተፉባት ትንግርት መሆኗን ተመልክተናል። ነገር ግን ፍለጋው በዚህ አላበቃም ይበልጡኑ ወደ ሥርዓተ ፀሐይ አድማሱን አስፍቷ በጥልቀት መቆፈሩን ቀጥሏል።

ማንኛውም ቴሌስኮፕ ከመሠራቱ፣ ቴክኖሎጂ ሰማዩን ከመንካቱ ከረጅም ጊዜ በፊት፣ ጥንት ቅድመ አያቶቻችን ከብዙ ሺ አመታት በፊት ስማቸውን በከዋክብት መካከል ጽፈው ነበር። ሳይንስ እንደ "አስትሮይድ" ያሉትን ቃላት ከማውጣቱ ቀደም ብሎ የአፍሪካ ቀደምት ህዝቦች ሰማያትን በጥልቀት ይመለከቱ ነበር። ካሲዮፒያ፣ሴፊየስ እና አንድሮሜዳ በተባሉት ነገስታት ስምም ታራካቸውን በሰማይ ህብረ ከዋክብት ላይ ላይሻር አሳርፈዋል። በሰማይ ላይ ያለ ነገር ሁሉ የሚያበራ ወይም የሚያንፀባርቅ አይደለም አንዳንዱ በጥልቅ ጨለማ ውስጥ እነሱን መመልከት እና መረዳት የሚችል ትክክለኛ አይኖችን በመጠበቅ በፀጥታ ይንቀሳቀሳሉ።

የዘመናዊ ሳይንስ አብይት በታበየበት እና አዳዲስ ግኝቶች በብዛት በፈለቁበት፣ በ19ኛው ክፍለ ዘመን መጀመሪያ ላይ የስነፈለክ ተመራማሪዎች ቴሌስኮፖቻቸውን በማርስና በጁፒተር መካከል ባለው ክፍተት ላይ በማነጣጠር አዲስ ነገርን አገኙ። እሱም ከሜትሮይድ የሚበልጥ፣ ፕላኔትም ሆነ ኮሜት ያልሆነ ነገር ሲሆን ለእርሱና ለመሰሎቹም “አስትሮይድ” የሚል ስያሜ ሰጧቸው።

"አስትሮይድ" የሚለው ቃል የመጣውም ከግሪክ ሲሆን፣ “ኮከብ መሰል” እንደማለት ነው፤ ይህ ስም የተመረጠው በቴሌስኮፖች አማካኝነት ሲታዩ እንደ ፕላኔቶች ክብ ቅርጽ ሳይሆን፣ እንደ ኮከብ የብርሃን ነጥቦች ሆነው ስለታዩ ነው።

ነገር ግን፣ ከጊዜ ወደ ጊዜ የነዚህ ነጥቦች ቁጥር እየበዛ መጣ ... 

ዛሬ ላይ 1.4 ሚሊዮን የሚደርሱ አስትሮይዶች እንዳሉ ተደርሶበታል። አብዛኛዎቹ አስትሮይዶችም በማርስ እና በጁፒተር መካከል በሚገኘው በዋናው የአስትሮይድ ቀለበት (main asteroid belt) ውስጥ በፀሀይ ዙሪያ ይከባሉ። አልፎ አልፎ እነዚ ትንንሽ አስትሮይዶች እና ኮሜቶች የግዙፍ ፕላኔቶች ስበት ሃይል ምክንያት ጥቂት ወደ ምድር አካባቢ ሊገፋ ይችላል። እነዚህን ነገሮችም በምድር አቅራቢያ ያሉ ነገሮች (NEOs ወይንም Near-Earth Objects) በመባል ይታወቃሉ። ከእነዚህ ውስጥ ወደ 99% የሚሆኑት አስትሮይዶች ናቸው።

በዘመናዊው የስነፈለክ ጥናት የሳይንሱ ሊቃውንት ዘመኑ በደረሰባቸው የቴክኖሎጂ ግኝቶች እና መሳሪያዎች በመጠቀም በአንድ ለሊት ብቻ በጣም ብዙ መረጃዎች ይሰበሰባሉ። ይህም በዓለም ዙሪያ ካሉ ቴሌስኮፖች በሙሉ የሚመጣውን ብዙ መረጃ በአንድ ጊዜ መተንተንና መከታተል አዳጋች ነው። ስለዚህም ተመራማሪዎቹ በሳይንሱ ዓለም ጉልህ ውሳኔ አድረጉ ይህም ምርምሩን ለህዝብ ክፍት በማድረግ ተማሪዎችን፣ መምህራን እና ራቅ ብለው ለማየት ፈቃደኛ የሆኑ ሰዎችን ከአለም ዙሪያ በመጋበዝ ዜጋ ተመራማሪዎች (Citizen Scientists) በሚል ስያሜ ስር ለአንድ ልዩ ተልዕኮ በመሰብሰብ የማይታወቀውን ነገር መፈለግ እና ከሌሎች እይታ ያመለጡትን ማደን ቀጥለዋል።

ዓለም አቀፍ የሥነ ፈለክ ፍለጋ ትብብር (IASC) ከፍተኛ ጥራት ያላቸውን የሰማይ አካላት መረጃዎች በአለም አቀፍ ደረጃቸውን ያጋራል። በዚህ የጥናትና ምርምር አውታረ መረብ ውስጥ፣ ፓን-አፍሪካ አስትሮይድ ፍለጋ ዘመቻ (PAN-Africa Asteroid Search Campaign) በአፍሪካ ለሚገኙ የሰማይ አካላት ተመልካቾች እና አዳኞች መኖሪያ ነው። በውስጡም የኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስ ሶሳይቲ በሚቆጣጠረው የኢትዮ-አስትሮይድ አዳኞች ቡድንን ጨምሮ ከአፍሪካ የመጡ የዜጋ ተመራማሪዎች ይገኛሉ።

የፓን-አፍሪካ የዜጋ ሳይንስ ላቦራቶሪ (PACS e-Lab) በአፍሪካ ውስጥ የሚገኙ የማወቅ ጉጉት ያላቸውን ተማሪዎች፣ መምህራን እንዲሁም የስነ ፈለክ ተመራማሪዎችን ከዘርፉ ባለሙያዎች ጋር በማስተሳሰር ወደ አለም አቀፍ ተወዳዳሪ ወደሆኑ አስትሮይድ አዳኞች ቀይሯቸዋል። ይህም የማወቅ ጉጉት ጥልቅ የሆነ የምርምር የወንድማማችነት ግንኙነት የሚፈጥር ነው።

ከሃምሳ (50) በሚበልጡ አገሮች የተውጣጡ ከአንድ ሺህ (1,000) በላይ በጎ ፈቃደኞች በየጊዜው በኮምፒውተር ስክሪኖቻቸው ፊት ይሰበሰባሉ። እንደ “ፓን-ስታርስ” ካሉ ቴሌስኮፖች የተገኙ የከዋክብት መረጃዎችን ይተነትናሉ። እነዚህ ተሳታፊዎች ኮምፒውተሮች ሊያመልጧቸው የሚችሉ ደካማና ተንቀሳቃሽ ነገሮችን ለመለየት እንደ አስትሮሜትሪካ ያሉ ሶፍትዌሮችን በመጠቀም ፍለጋ ያካሂዳሉ።

ይህ ጥረት እስካሁን ከመቶ ሰማኒያ አምስት (185) በላይ የሚሆኑ ጊዜያዊ የአስትሮይድ ግኝቶችን አበርክቷል ፣ እነዚህም ግኝቶች ወደ ናሳ ፕላኔታዊ የመከላከያ መረብ (NASA's planetary defense network) እንዲሁም ወደ ማይነር ፕላኔት ማዕከል (Minor Planet Center) እንዲገቡ ምክንያት ሆኗል። 

የኢትዮጵያ አስተዋጽዖ

Asteroid 2023 SY20 Orbit

በ2016 ዓ.ም ከመስከረም እስከ ጥቅምት ወር በተካሄደው የአስትሮይድ ፍለጋ ዘመቻ ወቅት፣ የኢትዮ-አስትሮይድ አዳኞች ቡድን ምልከታዊ መረጃን በማጥናት ለምርመራ የሚሆኑ ሁለት የሚንቀሳቀሱ አካላትን ዘገባ አድርጓል፤ እነዚህም አካላት የተለዩት በዜጋ ሳይንቲስቶቹ የተከናወነ ሲሆን፣ አነስተኛ ፕላኔት ማዕከል (Minor Planetary Center) እነዚህን ሪፖርቶች ከመረመረ በኋላ አነዚህን ሁለት ግኝቶች የመጀመሪያ የአስትሮይድ (Preliminary Asteroid) ብሎ አጽድቆ ነበር።

አንድ ዓመት ጥንቃቄ በተሞላበት ምልከታ እና የምህዋር ማረጋገጫ ጥበቃ በኋላ፣ ታኅሣሥ 3 ቀን 2017 ዓ.ም በአለም አቀፍ የስነ-ፈለከ ፍለጋ ትብብር (IASC) የኢትዮጵያን የመጀመሪያውን የምልምል አስትሮይድ ግኝት በይፋ በማረጋገጥ በአስትሮይድ 2023 SY20 ስም ሊመዘግበው በቅቷል።

አስትሮይድ 2023 SY20 ከተገኘበት ቦታ በ1.35 ሚሊዮን ኪሎ ሜትር በላይ ርቀት ላይ በፀሀይ ዙሪያ መዞሩን ቀጥሏል። ነገር ግን ትክክለኛው ጉዞው በህዋ ውስጥ ብቻ ሳይሆን በምድር ላይ ባለው የኢትዮጵያ ወጣት ትውልድ ወደ ከዋክብቱ እንዲደርስ በማነሳሳት የማወቅ ጉጉት-ትጋት እና ትብብር የአንድን ሀገር ታሪክ በሰማይ ላይ ሊጻፍ እንደሚችል ያረጋግጣል።

ከብዙ ሺህ ዓመታት በፊት አባቶቻችንም ታሪካቸውን እና ስማቸውን በሰማይ ላይ ቀርጸው ማስፈራቸውን እንደታሪክ ስንሰማ እና ድቅድቁን ጨለማ በጉጉት ስንመለከት ቆይተናል አሁን ግን ሰማይን ማንበብ ብቻ ሳይሆን የራሳችንን አሻራ ማሳረፍ ችለናል።

እና የሚቀረው ጥያቄ ቀላል ነው...

ቀጣዩን ማን ያገኝ ይሆን?

People Also Like