በታሪክ ታይተው የማይታወቁ ድንቅ የጠፈር ክስተቶች አሉ። ከእነዚህም ውስጥ ዋነኛው ከእኛ የፀሐይ ሥርዓት (Solar System) ውጭ ካሉ ሩቅ የከዋክብት ዓለማት ተነስተው የእኛን ስርዓተ-ፀሐይ የሚያቋርጡ "ኢንተርስቴላር አካላት" (Interstellar Objects) የሚባሉ አካላት ናቸው። እነዚህ አካላት በጋላክሲያችን ውስጥ ለቢሊዮን ዓመታት ሲንከራተቱ ቆይተው በአጋጣሚ ወደ እኛ ሰፈር ብቅ የሚሉ ሲሆኑ፣ በቅርቡ የተገኘው 3I/አትላስ (3I/ATLAS) የተሰኘው ኮሜት የዚህ ብርቅዬ ክስተት አካል ነው።

ኮሜት 3I/አትላስ (በዳን ባርሌት)
ኢንተርስቴላር ኮሜቶች ምንድን ናቸው?
አብዛኞቹ በሰማይ ላይ የምናያቸው ኮሜቶች እና አስትሮይዶች የራሳችን ፀሐይ ስበት ሰለባዎች ናቸው። ኢንተርስቴላር ኮሜቶች ግን ከእኛ የፀሐይ ሥርዓት ውጭ የተፈጠሩ እና በከዋክብት መካከል ያለውን ባዶ ቦታ አቋርጠው የሚመጡ መንገደኞች ናቸው። 3I/አትላስ ከመገኘቱ በፊት በታሪክ የታወቁት ሁለት ኢንተርስቴላር ኮሜቶች ብቻ ነበሩ፦ ኦሙአሙአ ('Oumuamua) በ2017 እ.ኤ.አ የተገኘው የመጀመሪያው እንግዳ ሲሆን፣ ቦሪሶቭ (Comet Borisov) ደግሞ በ2019 የተገኘው የመጀመሪያው ኢንተርስቴላር ኮሜት ነበር። 3I/አትላስ አሁን የዚህ ታሪካዊ ዝርዝር ሦስተኛው አባል ሆኗል።

ኮሜት ኦሙአሙአ፣ ኢንተርስቴላር አካሉ ኦሙአሙአ በምስሉ መሃል በሰማያዊ ተከቦ ይታያል። ቴሌስኮፑ ተንቀሳቃሹን ኮሜት ሲከታተል በዙሪያው ያሉት ከዋክብት የተለጠጠ መስመር መስለው ታይተዋል። (ESO/K. Meech et al.)(ግራ) ፤ ኮሜት ቦሪሶቭ፣ ሀብል በጥቅምት 2019 እ.ኤ.አ ከመሬት 418 ሚሊዮን ኪ.ሜ ርቀት ላይ የነበረውን ኮሜት 2I/ቦሪሶቭን እንዲህ ቀርጾታል። ምስሉ በኒውክሊየሱ ዙሪያ ያለውን አቧራ ቢያሳይም፣ ኒውክሊየሱ ራሱ ግን በጣም ትንሽ በመሆኑ በግልጽ አይታይም። (ናሳ/ESA)" (ቀኝ)
ከሌላ የፀሐይ ሥርዓት መምጣቱን እንዴት አወቅን?
ሳይንቲስቶች አንድ አካል ከውጭ የመጣ መሆኑን የሚያውቁት የሚጓዝበትን መንገድ ወይም "ምህዋሩን" (Orbit) በመለካት ነው።
የፍጥነት ልዩነት፦ በፀሐይ ሥርዓት ውስጥ ያሉ አካላት ፀሐይን የሚዞሩት በአንፃራዊነት ዝቅተኛ በሆነ አማካይ ፍጥነት በክብ ወይም ሞላላ መንገድ ነው። 3I/አትላስ ግን በሰዓት ከ240,000 ኪሎ ሜትር በላይ በሆነ እጅግ ከፍተኛ ፍጥነት ነው የሚጓዘው፣ ይህም የፀሐያችንን ስበት ተቋቁሞ ስርዓተፀሐያችንን ጥሶ ማለፍ እንዲችል ያደርገዋል።
ሀይፐርቦሊክ ምህዋር (Hyperbolic Trajectory)፦ ይህ ኮሜት የሚጓዝበት መንገድ "ሀይፐርቦሊክ" ይባላል፤ ይህም ማለት የፀሐይ ስበት ሊይዘው የማይችልበት እና ፍጥነቱ እጅግ ከፍተኛ በመሆኑ አንድ ጊዜ አልፎን ከሄደ በኋላ ዳግመኛ የማይመለስ መሆኑን ያረጋግጣል።
የጎዞ ታሪክ ክትትል፦ የኮሜቱን የጉዞ መስመር ወደ ኋላ በማስላት፣ ሳይንቲስቶች በግልጽ ከፀሐይ ሥርዓት ውጭ መነሳቱን አረጋግጠዋል።

በቬራ ሩቢን ኦብዘርቫቶሪ የታየው የ3I/አትላስ የዝግመተ ለውጥ ሂደት። አራቱ ምስሎች ኮሜቱ ከግኝቱ 10 ቀናት በፊት (ሰኔ 21) ጀምሮ እስከ ሐምሌ 19 ቀን 2025 እ.ኤ.አ የታየበትን ሁኔታ ሲያሳዩ፣ የላይኛው ክፍል ደግሞ በፀሐይ ሥርዓት ውስጥ ያለውን የጉዞ መስመር ያሳያል። (ምንጭ፦ NSF–DOE)
ለመሬት ስጋት ነው? ወይስ የባዕድ ፍጡራን (Alien) መንኮራኩር ይሆን?
እንዲህ ዓይነት እንግዳ አካላት ሲታዩ ብዙ ጊዜ ጭንቀት እና ግምቶች ይነሳሉ። እውነታው ግን እንደሚከተለው ነው፦
የ3I/አትላስ ምህዋር ከመሬት ጋር ምንም ዓይነት የመጋጨት እድል የለውም። ከመሬት ያለው በጣም ቅርብ ርቀት 260 ሚሊዮን ኪሎ ሜትር ሲሆን፣ ይህም መሬት ከፀሐይ ካላት ርቀት በእጥፍ ገደማ ይርቃል።
አንዳንድ ሰዎች የባዕድ ፍጡራን መንኮራኩር ሊሆን ይችላል ብለው ቢገምቱም፣ ሳይንቲስቶች ከ4,000 በላይ ምልከታዎችን በማድረግ ይህንን ውድቅ አድርገዋል። ኮሜቱ እንደ ማንኛውም ተፈጥሯዊ ኮሜት ጋዝ ያመነጫል፣ አቧራ ይረጫል፣ እና ጭራ አለው። ምንም ዓይነት የሬዲዮ ምልክት ወይም ሰው ሰራሽ የብርሃን ነጸብራቅ አልተገኘበትም።
ይህንን ኮሜት ለመመልከት የተደረጉ ትብብሮች እና ውጤቶች
ይህንን ኮሜት ለማጥናት ብዙ የጠፈር ተቋማት ተረባርበዋል፦
የቬራ ሩቢን ኦብዘርቫቶሪ፦ በምስል 3 ላይ እንደሚታየው፣ ኮሜቱ ከመገኘቱ 10 ቀናት በፊት (ሰኔ 21 ቀን 2025 እ.ኤ.አ) ጀምሮ የነበረውን የዝግመተ ለውጥ ሂደት መዝግቧል።
የJUICE መንኮራኩር፦ ወደ ጁፒተር በመጓዝ ላይ ያለው ይህ የአውሮፓ ጠፈር ኤጀንሲ (ESA) መንኮራኩር፣ በምስል 4 ላይ እንደሚታየው ኮሜቱ ለፀሐይ በጣም በቀረበበት ወቅት ድንቅ ፎቶግራፎችን አንስቷል። ምስሉ ኮሜቱ በጋዝ ደመና ተከቦ እና ረጅም ጭራ አውጥቶ በ0.44 AU (66 ሚሊዮን ኪሎ ሜትር) ርቀት ላይ ሲጓዝ ያሳያል።
የሀብል ስፔስ ቴሌስኮፕ፦ በህዳር 30 ቀን 2025 እ.ኤ.አ ኮሜቱን በቅርብ ተመልክቶ ጥናቱን አጠናክሯል።
ከዚህም በተጨማሪ የተለያዩ ተልዕኮዎች እና ሳተላይቶች የኮሜቱን ምስዕል ያነሱ ሲሆን ዝርዝሩን ከናሳ ድረ-ገጽ ይህንን በመጫን ማግኘት ይቻላል።

በJUICE፣ ሃብል፣ ጀምስዌብ እና ሉሲ ሚሽን የተነሱ የ3I/አትላስ ኮሜት ምስሎች
የዚህ ጥናት ሳይንሳዊ ዋጋ ምንድን ነው?
3I/አትላስን ማጥናት ማለት የሌላን የከዋክብት ሥርዓት ምስጢር እንደ መፍታት ነው።
የቁስ ናሙና፦ በኮሜቱ ውስጥ የሚገኙት ውሃ፣ ካርቦን ዳይኦክሳይድ እና ኦርጋኒክ ሞለኪውሎች ከእኛ ሥርዓት ውጭ ያሉ ፕላኔቶች እንዴት እንደሚፈጠሩ ፍንጭ ይሰጣሉ።
ሁለንተናዊ ተመሳሳይነት፦ የሚገርመው ነገር፣ ምንም እንኳን ከሩቅ ቢመጣም፣ 3I/አትላስ ልክ እንደ እኛ ኮሜቶች መሆኑ አጽናፈ ዓለም በሁሉም ቦታ ቁሶችን የሚሰራበት መንገድ ተመሳሳይ መሆኑን ያሳያል።
ማጠቃለያ
3I/አትላስ በአሁኑ ሰዓት ከፀሐይ እየራቀ ወደ መጣበት ጥልቅ የጠፈር ጨለማ በመጓዝ ላይ ነው። ዳግመኛ ወደ እኛ ባይመለስም፣ በቆይታው የሰጠን መረጃ ግን ስለ ሩቅ ዓለማት ያለንን እውቀት ለዘላለም የሚቀይር ነው።