Back to Blog

አርቴሚስ 2፡ የሃይድሮጂን ታንከሮች ፈተና እና ወደ ማርች የተሸጋገረው ታሪካዊው ጉዞ

አርቴሚስ 2፡ የሃይድሮጂን ታንከሮች ፈተና እና ወደ ማርች የተሸጋገረው ታሪካዊው ጉዞ

የሰው ልጅ ከግማሽ ምዕተ ዓመት በኋላ ወደ ጥልቅ ጠፈር ለመመለስ ያደረገው ዝግጅት የመጨረሻው ምዕራፍ ላይ ደርሷል። በፍሎሪዳ በሚገኘው የናሳ 39B ማስወንጨፊያ መድረክ ላይ፣ ግዙፉ 'ስፔስ ሎንች ሲስተም' (SLS) ሮኬት ለታሪክ ተዘጋጅቶ ቆሟል።

ነገር ግን፣ ይህ ታሪካዊ ጉዞ አልጋ በአልጋ አልሆነም። በቅርቡ የተደረገው ወሳኝ የነዳጅ ሙከራ (Wet Dress Rehearsal) በቴክኒካዊ ችግር ምክንያት በመቋረጡ፣ ቀደም ሲል ለፌብሩዋሪ 8 ታቅዶ የነበረው ማስወንጨፊያ አሁን ወደ ማርች 2026 እ.ኤ.አ ተሸጋግሯል። የናሳ መሐንዲሶች ይህንን የሃይድሮጂን ታንከሮች የማፍሰስ ፈተና ለመፍታት እና ለእያንዳንዱ ደቂቃ ዝርዝር እቅድ ለማውጣት ሌት ተቀን እየሰሩ ነው።

ይህ የ10 ቀናት ተልዕኮ "ወደ ጨረቃ ሄዶ መመለስ" ብቻ አይደለም፤ እጅግ ውስብስብ የሆኑ የጠፈር ምህዋር ቴክኒኮችን (Orbital Mechanics) እና የሰው ልጅን ስነ-ልቦና የሚፈትን ጉዞ ነው።


1. የአርቴሚስ ትውልድ፡ የጉዞው ዋና ተዋንያን

የቴክኖሎጂው ግዝፈት አስደናቂ ቢሆንም፣ የአርቴሚስ 2 ዋና የልብ ምት ግን ጠፈርተኞቹ ናቸው። ለዚህ ታሪካዊ ተልዕኮ የተመረጡት አራቱ ጠፈርተኞች ከአፖሎ ዘመን በተለየ መልኩ ዓለም አቀፋዊነትንና ብዝሃነትን ያንጸባርቃሉ።

  • ሬድ ዋይዝማን (አዛዥ): የቀድሞ የባህር ኃይል አብራሪ። "ዘመናዊ መንኮራኩሮች በአውቶማቲክ የሚሰሩ ቢሆኑም ለጥልቅ የጠፈር ኦፕሬሽኖች የሰው ልጅ ሚና ወሳኝ ነው" የሚል እምነት ያለው መሪ።
  • ቪክተር ግሎቨር (አብራሪ): በጨረቃ ዙሪያ በመጓዝ የመጀመሪያው ጥቁር ጠፈርተኛ በመሆን ታሪክ ይሰራል። የእሱ ሚና በምድር ምህዋር ውስጥ በሚደረጉ እንቅስቃሴዎች የመንኮራኩሯን የማሽከርከር ብቃት መከታተል ነው።
  • ክሪስቲና ኮክ (የተልዕኮ ስፔሻሊስት): በሴቶች የረጅም ጊዜ የጠፈር ቆይታ (328 ቀናት) ክብረ ወሰን የያዘችው ኮክ፣ ወደ ጥልቅ ጠፈር የምትጓዝ የመጀመሪያዋ ሴት ትሆናለች።
  • ጄረሚ ሀንሰን (የተልዕኮ ስፔሻሊስት): የካናዳ ስፔስ ኤጀንሲን (CSA) በመወከል፣ ከምድር ቅርብ ምህዋር ውጭ የሚጓዝ አሜሪካዊ ያልሆነ የመጀመሪያው ሰው።

የአርቴሚስ II የቡድን አባላት፦ በስተግራ ክርስቲና ኮክ፣ በስተጀርባ ቪክቶር ግሎቨር (ፓይለት)፣ በስተፊት ሪድ ዋይዝማን (አዛዥ)፣ በስተቀኝ ጄረሚ ሀንሰን (ናሳ)።

ከብቃት በላይ የሆነ ስብዕና

የናሳ ዋና ጠፈርተኛ (Chief Astronaut) ጆ አካባ ለ'Space.com' እንደገለጹት፣ የምርጫው መስፈርት ከቴክኒክ እውቀት ያልፋል፡

"በአንዲት ጠባብ ካፕሱል ውስጥ ለ10 ቀናት አብሮ ለመኖር፣ ቴክኒካዊ ብቃትህ ብቻ ሳይሆን፣ እንደ ሰው ያለህ ማንነት እና ባህሪ ወሳኝ ነው።"

2. ህይወት በ"ኢንተግሪቲ" ውስጥ፡ በጠፈር ላይ የሚንሳፈፍ ቤት

ይህንን ቡድን የምትሸከመው መንኮራኩር ከቀደሙት የጠፈር መንኮራኩሮች በእጅጉ የላቀች ናት። የመንኮራኩሩ አባላት ካፕሱሏን ለጠፈር ጉዞ የሚያስፈልገውን ስነ-ምግባራዊ ጽናት እና ታማኝነት እንዲወክል "ኢንተግሪቲ" (Integrity) ሲሉ ሰይመዋታል።

የተልዕኮው ስፔሻሊስት ክሪስቲና ኮክ መንኮራኩሯን "ለጥልቅ የጠፈር ጉዞ የሚሆን ተንቀሳቃሽ ቤት (RV)" ስትል ገልጻታለች። የውስጥ ክፍሉ የሁለት ሚኒባሶችን ያህል ስፋት ያለው ሲሆን፣ በምህንድስና ጥበብ ለተለያዩ አገልግሎቶች ተከፋፍሏል።

  • የውስጥ አቀማመጥ: አዛዡ እና አብራሪው በግራ በኩል ሆነው የመቆጣጠሪያ መሳሪያዎችን ሲያሽከረክሩ፣ የተልዕኮ ስፔሻሊስቶች ደግሞ በቀኝ በኩል ሆነው የበረራ መረጃዎችን ይከታተላሉ።
  • የዕለት ተዕለት ህይወት: የንጽህና መጠበቂያው (Hygiene bay) ከመግቢያው በር ወዲያውኑ በታች የሚገኝ ሲሆን፣ ጠፈርተኞቹ ከአንዱ ቦታ ወደ ሌላው ለመንቀሳቀስ የጡንቻ ጥንካሬን ለመጠበቅ የሚያገለግለውን የአካል ብቃት እንቅስቃሴ መሳሪያ በመዝለል ማለፍ አለባቸው።

ጥንካሬ: አዛዥ ዋይዝማን እንዳሉት፣ "ኬብሎቹ እንኳን ሳይቀር ከሚያስፈልገው በላይ ወፍራም" መስለው መሰራታቸው ለጉዞው ስነ-ልቦናዊ እና አካላዊ ዋስትና ይሰጣል።

የጠፈር ልብስ መሐንዲሶች በጆንሰን የጠፈር ማዕከል ውስጥ የመንኮራኩሩን ሞዴል በመጠቀም፣ አራት የቡድን አባላት በኦራይን (Orion) መንኮራኩር ውስጥ ለውንጨፋ እንዴት እንደሚቀመጡ ማሳያ እያቀረቡ ( NASA/Robert Markowitz)

3. የተልዕኮው ዝርዝር፡ በደቂቃዎች የተሰላ የጉዞ እቅድ

ጉዞው በአራት ዋና ዋና እና ወሳኝ ምዕራፎች የተከፈለ ነው፡

ምዕራፍ 1፡ መወንጨፍ እና የ"ICPS" ሚና (የመጀመሪያዎቹ 40 ደቂቃዎች)

ሮኬቱ ከተወንጨፈ በኋላ ጉዞው ቀጥታ ወደ ጨረቃ አይደለም። ከተተኮሱ ከ40 ደቂቃዎች በኋላ፣ የሮኬቱ የላይኛው ክፍል (ICPS - Interim Cryogenic Propulsion Stage) ሞተሩን በማስነሳት የመንኮራኩሯን ምህዋር ከፍ ያደርገዋል። ይህ የመጀመሪያው ወሳኝ እርምጃ ነው።

ይህ ምስላዊ መግለጫ የአርቴሚስ II የሙከራ በረራ በሚከናወንበት ወቅት፣ የኤስ.ኤል.ኤስ (SLS) ሮኬት እና የኦራይን መንኮራኩር ከመነሻ (ማስወንጨፍ) ጀምሮ ወደ ጠፈር እስከሚወጡበት ጊዜ ድረስ፣ እንዲሁም የኦራይንን የፔሪጂ ከፍታ ማስተካከያ ሞተር ቃጠሎ (perigee raise burn) ጨምሮ የቁልፍ ክንውኖችን ጊዜ፣ ፍጥነት እና ከፍታ ያሳያል። (ናሳ)

ምዕራፍ 2፡ የ42 ሰዓታት "የምድር ላይ" ፍተሻ (The Test Drive)

አርቴሚስ 2 ከሌሎች ተልዕኮዎች የሚለየው እዚህ ላይ ነው። መንኮራኩሯ ምድርን በኤሊፕቲካል (እንቁላል ቅርጽ) ምህዋር እየዞረች ለ42 ሰዓታት (ለ2 ቀናት ያህል) ትቆያለች።

  • ከፍታ: በዚህ ወቅት ከምድር በዝቅተኛው 185 ኪ.ሜ እንዲሁም በከፍተኛው 2,600 ኪ.ሜ ርቀት ላይ ትገኛለች።
  • ግቡ: ይህ ልክ አዲስ መኪና ገዝቶ ለረጅም ጉዞ ከመውጣት በፊት በሰፈር ውስጥ እንደመንዳት ነው። በዚህ ሰዓት ውስጥ አብራሪው ቪክተር ግሎቨር እና ቡድኑ የህይወት አድን ስርዓቱን (Life Support) እና የመንኮራኩሯን የማሽከርከር አቅም በእጅ (Manually) ይፈትሻሉ። ሁሉም ነገር አስተማማኝ ካልሆነ፣ ወደ ጨረቃ ሳይሄዱ በቀላሉ ወደ ምድር መመለስ ይችላሉ።

የአርቴሚስ 2 የጉዞ ዝርዝር መግለጫ (ናሳ)

ምዕራፍ 3፡ ወደ ጨረቃ እና "የድብልቅ ነጻ-መመለስ ምህዋር"

ሁሉም ነገር አስተማማኝ መሆኑ ከተረጋገጠ በኋላ፣ ዋናው ጉዞ ይጀምራል። የሮኬቱ ሞተር በኃይል በመነሳት መንኮራኩሯን ወደ ጨረቃ ይገፋታል። የሚከተሉት መንገድ "ሃይብሪድ ፍሪ-ሪተርን" (Hybrid Free-Return Trajectory) ይባላል።

  • ምን ማለት ነው? ይህ የመንኮራኩሯ ሞተር ቢበላሽ እንኳን፣ የተፈጥሮን የጨረቃ ስበት ኃይል (Gravity) ብቻ በመጠቀም መንኮራኩሯን እንደ "ወንጭፍ" (Slingshot) ወርውሮ ወደ ምድር የሚመልስ ዘዴ ነው። ይህ ለጠፈርተኞቹ ደህንነት ሲባል የተመረጠ ብልህ መንገድ ነው።



አዲስ ክብረ ወሰን: መንኮራኩሯ ከጨረቃ ገጽታ በስተጀርባ 8,889 ኪሎ ሜትር (5,523 ማይሎች) ትርቃለች። በዚህ ወቅት ከምድር ያላቸው አጠቃላይ ርቀት ከ400,000 ኪሎ ሜትር በላይ ይሆናል።

ከዚህ ከፍተኛ ከፍታ ካለው ምቹ ቦታ፣ ጠፈርተኞቹ ሙሉውን የጨረቃ ገጽ አስቸጋሪ የሆኑትን ሰሜንና ደቡብ ዋልታዎችን ጨምሮ—በአንድ ጊዜ ማየት ይችላሉ። ጨረቃ በጣም በምትቀርብበት ወቅት፣ እጅን ዘርግቶ እንደተያዘ የቅርጫት ኳስ ያህል ግዙፍ ሆና ትታያለች። (NASA Goddard/CI Lab)

ምዕራፍ 4፡ መመለስ እና የእሳት ፈተና (Heat Shield Challenge)

ወደ ምድር መመለስ ከጉዞው ሁሉ እጅግ አደገኛው ክፍል ነው። መንኮራኩሯ በሰዓት 40,000 ኪሎ ሜትር በሚደርስ ፍጥነት ወደ ምድር የአየር ክልል ስትገባ፣ የውጪው ክፍል እስከ 2,700 ዲግሪ ሴልሺየስ ይሞቃል።

  • ችግሩ: በአርቴሚስ 1 ተልዕኮ ላይ፣ የሙቀት መከላከያ ጋሻው (Avcoat) ባልተጠበቀ ሁኔታ ተቃጥሎ እና ተሰነጣጥቆ ነበር። ምክንያቱም በአምራችነት ሂደት የታቀበ ጋዝ ስለነበር ነው።
  • መፍትሄው: ናሳ ጋሻውን ሙሉ ለሙሉ ከመቀየር (ይህ ዓመታትን ይወስዳል)፣ የበራራ መስመሩን (Trajectory) ቀይሮታል። አዲሱ መስመር ሙቀቱን በተሻለ መንገድ እንዲሰራጭ በማድረግ ጋሻው እንዳይጎዳ ይከላከላል።

4. ወቅታዊ ሁኔታ፡ የሃይድሮጂን መፍሰስ እና ወደ ማርች የተደረገ ሽግግር

ቀደም ሲል ናሳ የማስወንጨፊያ ቀኑን ለፌብሩዋሪ 8 አቅዶ የነበረ ቢሆንም፣ አሁን ግን ሁኔታዎች ተቀይረዋል። በኬኔዲ ስፔስ ሴንተር በተደረገው የነዳጅ ሙከራ (Wet Dress Rehearsal) ወቅት፣ መሐንዲሶች በሮኬቱ ዋና አካል ላይ ቴክኒካዊ ችግር አጋጥሟቸዋል።

ችግሩ ምንድን ነው?

ወደ ሮኬቱ 2.65 ሚሊዮን ሊትር የሚሆን እጅግ ቀዝቃዛ ነዳጅ (Super-cold propellant) በመሙላት ላይ እያሉ፣ የከርሰ ምድር ቡድኖች የፈሳሽ ሃይድሮጂን መፍሰስ (Liquid Hydrogen leak) ምልክት አይተዋል። ሃይድሮጂን እጅግ በጣም ቀዝቃዛ ከመሆኑ የተነሳ የሮኬቱን ማያያዣዎች (Seals) በማኮማተር በትንሹም ክፍተት ሾልኮ የመውጣት ባህሪ አለው።

ሙሉ ጨረቃ በናሳ የኤስ.ኤል.ኤስ (SLS) ሮኬት እና ኦራይን መንኮራኩር ላይ ስታበራ፤ የካቲት 1 ቀን 2026 ዓ.ም. (እ.ኤ.አ)። ሮኬቱ በአሁኑ ወቅት በፍሎሪዳ በሚገኘው ኬኔዲ የጠፈር ማዕከል "Launch Pad 39B" ላይ ይገኛል። የቴክኒክ ቡድኑ ለአርቴሚስ II ውንጨፋ ዝግጅት እንዲሆን "Wet Dress Rehearsal" የተሰኘውን የሙከራ ልምምድ በማከናወን ላይ ነው። (ናሳ/ሳም ሎት)

ውሳኔው

ይህ ችግር ቀላል ቢመስልም፣ ናሳ በጠፈርተኞቹ ህይወት ላይ ምንም አይነት አደጋ ላለመውሰድ ሲል ሙከራውን አቋርጧል። ችግሩን ለመፍታት እና አስፈላጊውን ጥገና ለማድረግ ሲባልም፣ የማስወንጨፊያ ቀኑ ወደ ማርች 2026 ተሸጋግሯል። ይህ ተጨማሪ ጊዜ ቡድኑ ቫልቮችን እንዲጠግን እና ስርዓቱን እንደገና እንዲፈትሽ እድል ይሰጣል።

5. የወደፊቱ እውነታ፡ አርቴሚስ 3 እና የተግዳሮት ድምጾች

አርቴሚስ 2 ለቀጣዩ የአርቴሚስ 3 ተልዕኮ (የሰው ልጅ በጨረቃ ላይ የሚያርፍበት) መንገድ ጠራጊ ነው። ናሳ አርቴሚስ 3ን በ2027 ለማከናወን ቢያቅድም፣ የናሳ ኢንስፔክተር ጄኔራል ቢሮ ግን በዚህ የጊዜ ሰሌዳ ላይ ጥርጣሬ አለው።

ዘገባዎች እንደሚያመለክቱት፣ ለዚህ ስጋት ዋና ምክንያቶች፡-

  1. Starship: የSpaceX ግዙፍ ሮኬት (የሰውን ልጅ ጨረቃ ላይ የሚያሳርፈው) አሁንም በሙከራ ሂደት ላይ መሆኑ፣ እና
  2. የጠፈር ልብሶች (Spacesuits): በጨረቃ ላይ ለመራመድ የሚያስችሉ አዳዲስ የጠፈር ልብሶች ዝግጅት መጓተት ናቸው።

ስለዚህ፣ የአርቴሚስ 2 ስኬት፣ እነዚህን ቀጣይ ተግዳሮቶች ለመፍታት እና ጉዞውን ወደፊት ለማስቀጠል ወሳኝ ሚና ይጫወታል።

መደምደሚያ

ይህ ሁሉ ጥረት ለአንድ ትልቅ ግብ ነው፣ ማርስ። ጨረቃ ለሰው ልጅ እንደ መለማመጃ እና እንደ ነዳጅ ማደያ ጣቢያ ታገለግላለች። እንዲሁም በዚህ ተልዕኮ የሚሞከረው O2O (Optical Communications System) የተሰኘው የሌዘር ቴክኖሎጂ፣ ከጨረቃ ሆነው ጥርት ያለ የ4K ቪዲዮ ወደ ምድር ማስተላለፍ ያስችላል።

አርቴሚስ 2፣ የሰው ልጅ "ጎብኚ" ብቻ ሳይሆን የጠፈር "ነዋሪ" ለመሆን የሚያደርገው ጉዞ የመጀመሪያው፣ ትልቁ እና የማይተካው እርምጃ ነው።


🔗 Sources

ናሳ (NASA): የአርቴሚስ 2 ኦፊሴላዊ ፕሬስ ኪት፣ የተልዕኮው ዝርዝር እቅድ እና መረጃዎች። https://www.nasa.gov/artemis-ii-press-kit/ ስፔስ ዶት ኮም (Space.com): ስለ 8,889 ኪ.ሜ ርቀት፣ የጠፈርተኞች ምርጫ እና የናሳ ዋና ጠፈርተኛ ጆ አቃባ ቃለ-መጠይቅ። https://www.space.com/artemis-2-humans-moon-orbit ዩኒቨርስ ቱዴይ (Universe Today): ስለ ሮኬቱ ቅድመ-ዝግጅት እና የነዳጅ ሙከራ ሂደቶች። https://www.universetoday.com/articles/nasa-enters-final-preparations-for-artemis-ii-mission ሲኤንኤን (CNN): ስለ ኦርዮን የሙቀት መከላከያ ጋሻ (Heat Shield) ችግሮች እና የምህንድስና መፍትሄዎች። https://edition.cnn.com/2026/01/23/science/artemis-2-orion-capsule-heat-shield የናሳ ወቅታዊ መግለጫዎች (NASA Blogs): ስለ ሃይድሮጂን መፍሰስ እና የጊዜ ሰሌዳ ለውጥ። https://blogs.nasa.gov/artemis/

People Also Like