እ.ኤ.አ. በ1960ዎቹ የሰው ልጅ በወቅቱ በነበረው ውስን የኮምፒውተር ቴክኖሎጂ ተጠቅሞ ጨረቃ ላይ ያረፈበት መንገድ፣ ሂደቱን ቀላል አስመስሎት ነበር። በአንጻሩ፣ በዘመናዊ ቴክኖሎጂ የተደራጀው የአሜሪካ ብሔራዊ የጠፈር እና ኤሮኖቲክስ አስተዳደር (ናሳ)፣ ዛሬ ያንን ታሪክ ለመድገም ከፍተኛ ተግዳሮት ገጥሞታል። ለዚህ መዘግየት እና ውስብስብነት ዋነኛው ምክንያት የቴክኖሎጂ እጦት ሳይሆን፣ የዓላማ፣ የስትራቴጂ እና የጂኦፖለቲካዊ አውድ ለውጥ ነው።
በቅርቡ ናሳ ይፋ እንዳደረገው፣ የአርቴምስ II ተልዕኮን ለማስጀመር እየተደረገ ያለው ዝግጅት በተለያዩ ቴክኒካዊ እና ስትራቴጂካዊ ምክንያቶች የማስተካከያ ጊዜዎችን አስተናግዷል። በተቋሙ የቅርብ ጊዜ ሪፖርት መሰረት፣ ለቀጣዩ የማምጠቅ ሙከራ የታቀደው ጊዜ የካቲት/መጋቢት 2018 ዓ.ም (March 2026) ነው።
1. ታሪካዊ የጠፈር ፉክክር ዳራ፡ ከስፑትኒክ እስከ አፖሎ
የአፖሎ ፕሮግራም የተፀነሰው ከንጹህ ሳይንሳዊ ፍላጎት ይልቅ፣ በወቅቱ ከነበረው የህልውና ስጋት እና የፖለቲካ የበላይነት ፉክክር ነበር።
- የሶቭየት ህብረት የበላይነት፡ የቀድሞዋ ሶቭየት ህብረት ስፑትኒክን ወደ ምህዋር በማምጠቅ፣ ተከትላም ላይካ የተሰኘችውን ውሻ እና ዩሪ ጋጋሪንን ወደ ጠፈር በመላክ የቴክኖሎጂ የበላይነቷን ማረጋገጧ ለአሜሪካ መንግስት ከባድ የደህንነት እና የፖለቲካ ጫና ፈጥሮ ነበር።

ምስል 1፦ ላይካ በግራ ስፑትኒክ በቀኝ
- የአሜሪካ ስትራቴጂካዊ ምላሽ፡ ናሳ የተመሰረተው ይህንን የኃይል ሚዛን ለመቀልበስ ነው። ፕሬዝዳንት ጆን ኤፍ. ኬኔዲ
"በዚህ አስርት ዓመት መጨረሻ የሰው ልጅን ጨረቃ ላይ እናሳርፋለን" ሲሉ ያደረጉት ንግግር፣ አሜሪካ ከሶቭየት ህብረት የላቀች መሆኗን ለማረጋገጥ የታቀደ ፖለቲካዊ ውሳኔ ነበር።
በዚህም ምክንያት ያልተገደበ በጀት ተመደበ። በቁጥር ሲሰላ፣ በ1966 እ.ኤ.አ. በአፖሎ ፕሮግራም ማብቂያ አካባቢ የናሳ በጀት የሀገሪቱን አጠቃላይ በጀት 4.4% ይሸፍን ነበር። ይህን ወደ 2024 የገንዘብ ዋጋ ስንቀይረው በዓመት 68 ቢሊዮን ዶላር ገደማ ነበር። በአንጻሩ በአሁኑ ወቅት ለናሳ የሚመደበው በጀት ከጠቅላላው የሀገሪቱ በጀት 0.4% ብቻ ሲሆን፣ ይህም ወደ 25 ቢሊዮን ዶላር ገደማ ነው።
የበጀት ንፅፅር (የዋጋ ግሽበት ታሳቢ ሲደረግ):
- 1966 (አፖሎ): ████████████████████ $68 ቢሊዮን
- 2024 (አርቴምስ): ███████ $25 ቢሊዮን

ምስል 2፦ የናሳ በጀት ከአሜሪካ የፌዴራል መንግስት በጀት በመቶኛ ንጻሬ
ከዚህ የገንዘብ ልዩነት ባሻገር፣ በ1960ዎቹ የናሳ በጀት እና ትኩረት ሙሉ ለሙሉ ወደ አንድ አላማ (አፖሎ) ያዘነበለ ነበር። በአሁኑ ጊዜ ግን ተቋሙ የተበታተነ የትኩረት አቅጣጫ አለው። ይህ ውስን በጀት ለዓለም አቀፍ የጠፈር ጣቢያ፣ ለማርስ ጥናት፣ ለጄምስ ዌብ ቴሌስኮፕ እና ለሌሎችም ሳይንሳዊ ፕሮጀክቶች ይከፋፈላል። ስለዚህ ለአርቴምስ ፕሮግራም የሚደርሰው የሀብት ድርሻ ከአፖሎ ጋር ሲነፃፀር እጅግ አነስተኛ ነው።
2. የጠፉ ክህሎቶች እና የፈራረሱ መሰረተ ልማቶች
የአፖሎ ተልዕኮ ስኬትን ተከትሎ፣ የአሜሪካው ምክር ቤት ፖለቲከኞች የናሳን በጀት ከመቀነስ አንስቶ የአፖሎ መረሃግብሮችን መሰረዛቸው ኹለተኛው ምክንያት ነው።
በወቅቱ የናሳ አስተዳዳሪ የነበሩት ጄምስ ዌብ "የተገነባው የቴክኖሎጂ አቅም እንዳይባክን ፕሮግራሙ መቀጠል አለበት" የሚል መከራከሪያ ቢያቀርቡም ተቀባይነት አላገኙም። ይህ ውሳኔ የሚከተሉትን አሉታዊ ውጤቶች አስከትሏል፡
- የሰው ኃይል መበተን: ለፕሮጀክቱ ይረባረቡ የነበሩ 400,000 (አራት መቶ ሺህ) የሚሆኑ ከፍተኛ ባለሙያዎች፣ ኢንጂነሮች እና ሳይንቲስቶች ተበተኑ። እነዚህ ባለሙያዎች ያካበቱት ወሳኝ የልምድ እውቀት እና ተቋማዊ ልምድ አብሮ ሊጠፋ ችሏል።
- የኢንዱስትሪ መውደም: ታዋቂውን የሳተርን 5 ሮኬት መለዋወጫ ያቀርቡ የነበሩ በሺዎች የሚቆጠሩ ፋብሪካዎች ተዘጉ። ለምሳሌ በኒው ኦርሊንስ የሚገኘውና ከ30 በላይ የእግር ኳስ ሜዳዎችን የሚያህል ስፋት ያለው ሚሹድ የመገጣጠሚያ ተቋም፣ ምንም እንኳን በኋላ ላይ ለስፔስ ሻትል (Space Shuttle) የውጭ ታንከሮች እና አሁን ለአርቴምስ አገልግሎት እየሰጠ ቢሆንም፣ በወቅቱ የሳተርን 5 ሮኬቶችን ያመርትበት የነበረው ልዩ የመገጣጠሚያ የሥራ ሂደት እና መሳሪያዎች ግን ለሌላ አገልግሎት እንዲውሉ ተደርገዋል ወይም ተወግደዋል።

ምስል 3፦ የሳተርን V መንኮራኩር
ስለሆነም፣ የአሁኑ ትውልድ ፈተና ቀደም ሲል የተሰራን ስራ እንደ አዲስ የመጀመር ጉዳይ ነው። ያንን ታሪክ የሰሩት እጆች ዛሬ በህይወት የሉም፤ አብዛኞቹ በጡረታ ወይም በሞት ተለይተዋል። ምንም እንኳን የሰነድ ማስረጃዎች ቢኖሩም፣ የተግባር እውቀት እና የሂደት ልምድ በሰነድ ብቻ ሊተካ አይችልም።
3. የአሁኑ የጠፈር ፉክክር እና የቻይና ሚና
የሶቭየት ህብረት መፍረስን ተከትሎ፣ የጠፈር ፉክክር ቀዝቅዞ ነበር። አሜሪካ እና ሩሲያ በዓለም አቀፍ የጠፈር ጣቢያ በትብብር መስራት ጀመሩ። ታዲያ የአርቴምስ ፕሮግራም አስፈላጊነት ለምን አሁን ጎላ?
መልሱ የቻይና ፈጣን የቴክኖሎጂ እድገት ነው።
ቻይና ወደዚህ ፉክክር የገባችው በምርጫዋ ብቻ አልነበረም። አሜሪካ በብሔራዊ ደህንነት ስጋት ምክንያት ቻይናን በዓለም አቀፍ የጠፈር ጣቢያ እንዳትሳተፍ አግዳት ነበር። ይህ እገዳ ቻይናን ከማዳከም ይልቅ፣ የራሷን የጠፈር ጣቢያ (ቲያንጎንግ) በራሷ አቅም እንድትገነባ ገፋፍቷታል። ቻይና በጨረቃ የጀርባ ክፍል ላይ በማረፍ እና የአፈር ናሙና በመመለስ ያስመዘገበችው ስኬት፣ አሜሪካን ለዳግም የጠፈር የበላይነት ፉክክር አነሳስቷታል።

ምስል 4፦ የቻይና የጠፈር ጣቢያ (ቲያንጎንግ)
ይህንን ስጋት መሰረት በማድረግ እ.ኤ.አ በ2017 ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ "እኛ መሪ ነን፣ መሪም ሆነን እንቀጥላለን፣ ይህንንም በብዙ እጥፍ እናሳድገዋለን" በማለት የአርቴምስን ፕሮግራም በይፋ አስጀመሩ። በመሆኑም ለአርቴምስ መወለድ የቻይና ተጽእኖ ከፍተኛ ድርሻ አለው።
4. የአርቴምስ ተልዕኮ ስትራቴጂያዊ ተግዳሮቶች
በአሁኑ ወቅት ወደ ጨረቃ መመለስ የከበደበት ምክንያት በሶስት አበይት ጉዳዮች ይገለጻል፡
ሀ. የደህንነት እና የአደጋ ስጋት አስተዳደር
እ.ኤ.አ በ1960ዎቹ "ከሩሲያ ለመቅደም ማንኛውንም መስዋዕትነት እንከፍላለን" የሚል ከፍተኛ የአደጋ ተቀባይነት መንፈስ ነበር። በአሁኑ ዘመን ግን ናሳ በማንኛውም ተልዕኮ ላይ የሰው ህይወት እንዳይጠፋ ከፍተኛ ጥንቃቄ ያደርጋል። እያንዳንዱ ስርዓት በተደጋጋሚ መፈተሽ አለበት። ይህ የ"ዜሮ ስህተት" አካሄድ ከፍተኛ ጊዜ እና ወጪን ይጠይቃል።
ለ. የዘላቂነት መርህ
የአፖሎ ዓላማ የፖለቲካ የበላይነትን ማረጋገጥ እና መመለስ ነበር። የአርቴምስ ዓላማ ግን በጨረቃ ላይ ቋሚ መሠረት መጣል ነው።
- የአርቴምስ ኦራዮን መንኮራኩር በጨረቃ ምህዋር ውስጥ ለሳምንታት የመቆየት አቅም ሊኖራት ይገባል።
- የሚገነቡት የምህዋር ጣቢያዎች እና ማረፊያዎች እንደገና ጥቅም ላይ የሚውሉ እና ዘላቂ አገልግሎት የሚሰጡ መሆን አለባቸው።
ሐ. የተፈጥሮ ህግጋት እና የጊዜ ሰሌዳ
ምንም እንኳን ቴክኖሎጂው ቢኖርም፣ የተፈጥሮን ህግ ማሸነፍ እና መተላለፍ አይቻልም። ናሳ በቅርቡ ባወጣው የArtemis II Mission Availability ሪፖርት መሰረት፣ መንኮራኩሯን ለማምጠቅ የምድር እና የጨረቃ አቀማመጥ፣ እንዲሁም የብርሃን ሁኔታ መጣጣም አለባቸው።
ለምሳሌ በየካቲት/መጋቢት 2018 ዓ.ም. ናሳ ያለው እድል ውስን ነው፡
- ከየካቲት 27-29 (March 6-8): ምቹ ቀናት ናቸው።
- ከየካቲት 30 - መጋቢት 3 (March 9-12): በጣም ጥሩ እድል አለ።
- ከዚያ በኋላ ግን እስከ መጋቢት 23 (April 1) ድረስ መስኮቱ ይዘጋል።

ምስል 5፦ የአርቴምስ ኹለት ምልምል ጠፈርተኞች
ማጠቃለያ
ወደ ጨረቃ የሚደረገው ጉዞ ፈተና የሰው ልጅ አቅም ማነስ ሳይሆን፣ የተቋረጠ የእውቀት ቅብብሎሽ እና የዓላማ ለውጥ ውጤት ነው። ያኔ የነበረው ግብ አጭር ጊዜ ድል ሲሆን፣ የአሁኑ ግብ ዘላቂ የጠፈር ሰፈራ ነው። የቀድሞው ትውልድ በብሔራዊ ርብርብ የሰራውን ታሪክ፣ ዛሬ በተወሰነ በጀት እና በጥብቅ የደህንነት መስፈርቶች እንደገና መገንባት ከባድ ፈተና ነው። ሆኖም የቻይና ወደ መድረኩ መምጣት ውድድሩን ስላቀጣጠለው፣ የሰው ልጅ በቅርቡ ጨረቃን መልሶ እንደሚረግጥ አያጠራጥርም።